የምክር ቤቱ የተመራጭ ሴቶች ኮከስ የተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ64 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

የምክር ቤቱ የተመራጭ ሴቶች ኮከስ የተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ64 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራጭ ሴቶች ኮከስ የተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 64 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በዓይነት እና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡
ኮከሱ ዛሬ የ2012 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በመገምገም የ2013 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህ ወቅት የኮከሱ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኸኝ እንዳሉት÷ በፀጥታ ችግር፣ በኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁም በጎርፍ አደጋ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የኀብረተሰብ ክፍሎች የተደረጉት ድጋፎች ከተለያዩ ምግባረ-ሰናይ ተቋማት በኮከሱ አማካይነት ተሰባስበው በተለያዩ የሃገሪቱ ቦታዎች ለሚገኙ ተጎጂዎች የተበረከቱ ናቸው፡፡
በሪፖርቱ እንደተመለከተውም 47 ሚሊየን ብር የሚገመት ሀብት በዓይነት እና 17 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ በማሰባሰብ ጉዳት ለደረሰባቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ሰብሳቢዋ አያይዘውም በኮሮና ወረርሽኝ እና በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ኮከሱ ያቀዳቸው ሥራዎች በዕቅዱ ልክ አለመከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የአቅም ግንባታ ሥራ በተወሰነ መልኩ መከናወኑን እና በአፋር ክልል ብቻ ኮከስን የማጠናከር ሥራ መከናወኑን ሰብሳቢዋ ማስታወሳቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

The post የምክር ቤቱ የተመራጭ ሴቶች ኮከስ የተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ64 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply