የምግብ ዓይነቶችን ከቀየሩ ከወር በላይ ሆኗቸዋል፤ “ለምን የሚል ይባረራል”- የዲላና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 

የማስታወቂያው ቀን ስህተት አለው- ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 

ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቅጥር ግቢያቸው ውስጥ ለተማሪዎች በተለጠፈ ማስታወቂያ “እንደአገር ባጋጠመን የምግብ በጀት እጥረት” እና “የምግብ ጥሬ ዕቃ ዋጋ በየቀቡ መጨመር” ሳቢያ የምግብ ዓይነቶች እንደሚቀየሩ በማስታወቂያ መግለጻቸውን የሚያሳዩ ምስሎችን አዲስ ማለዳ ተመክታለች።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “ባለፈው ሳምንት ማስታወቂያ ያውጣ እንጂ ከሶስት ወር በፊት ነው የተጀመረው [የምግብ መቀየሩ]። ትምህርታችን ይቅደም ብለን ነው እንጂ ከባድ ሁኔታ ነው ያለው በጊቢው ውስጥ” ብለዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በበኩላቸው ይህ የምግብ ፕሮግራም ከተቀየረ ከአንድ ወር በላይ እንደሚሆነው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

“ለውጥ እንዳማናመጣ ስላወቅን” እስካሁን ምንም አይነት አድማ ሆነ ሰልማዊ ሰልፍ አላደረግንም የሚሉት የዲላዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ሲጠይቁ “ በጀት የለም ከኪሳችን ነው እየመግብናችው ነው ያለነው ስለዚህ የቀረበውን ተመገቡ” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ተማሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።  አዲስ ማለዳ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችን ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። 

ዩኒቨርሲቲው መጋቢት 26 ቀን 2016 ባወጣው ማስታወቂያ “ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ” በማከማቻ )ስቶር) ከሚገኙ የምግብ ጥሬ ዕቃዎች እና አትክልት በመጠቀም ምግብ እያቀረበ መሆኑን ገልጾ አስቸኳይ ግዢ እንዲፈጸም ጠይቄያለሁ ይላል። ተማሪዎቹ በበኩላቸው “የምንመገበው አንዳይነት ምግብ ነው። በተከታታይ ጥቅል ጎመን እና ሽሮ፤ በዛላይ እንደሚታወቀው ባግባቡም አይሰራም በጣም ችግር ላይ ነው ያለነው” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል። 

“ምን እየተፈጠረ እንደሆነ እኛም እየገባን አይደለም” የሚሉት ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚገኙት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “ለምን እንደዚህ ሆነ የሚል ጥያቄ እንኳን ቢነሳ ጊቢው ያባርራል” በማለት አንድ የተማሪ የሚፈጸሙ ልክ ያሉ ነገሮችን ላይ ጥያቄ በማንሳቱ “ከፖለቲካ ጋር አያይዘው አባረውታል” በማለት ነግረውናል። 

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የተማሪዎችን ምገባ በተመለከተ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ታሳቢ ባደረገ መልኩ፤ የምግብ ጥራትን እና ብዛትን ሳያጓድል ከተማሪዎች ሕብረት አመራር አካላት ጋር እንዲሁም ከአብዛኛው ተማሪ ጋር በመወያየት ከወራት በፊት የተደረገ የሜኑ ማሻሻያ ለማሳወቅ ማስታወቂያ ያወጣ ሲሆን፤ ይህም የቀን ስህተት የነበረበት መሆኑን እና አዲስ የተደረገ የሜኑ ለውጥ እንደሌለ እንገልጻለን” ብሏል።

እንደወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መግለጫ ከሆነ ድርጊቶቹ “የተቋሙን በጎ ገጽታ ለማጠልሸት እና የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ” የተፈጸሙ ናቸው። 

ከምግብ ዝርዝር ውስጥ ስጋ ከወጣ ቆይቷል የሚሉት ተማሪዎቹ በፊት ቁርስ ላይ ፍርፍር ይቀርብ እንደነበር በመግለጽ አሁን ቁርስ አንድ ‘ዳቦ’፤ ምሳ እና እራት ‘ሽሮ’ እንደሚቀርብላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ህብረት ፕሬዝዳንት “የዩንቨርስቲው ፕሬዚዳንት እንደተመረጠ” የተናገሩት ተማሪዎች “ለተማሪ ጭራሽ የማይቆም ሆኗል” ሲሉ ድምጽ ሊሆናቸው እንዳልቻለ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

“ለመማር ስንል ያለን አማራጭ መቆየት ነው” ያሉት ተማሪዎቹ የተወሰኑ ተመራቂ ተማሪዎች ከመመረቂያ ጊዜ መራዘም እና ካለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች አሉ ብለዋል። አዲስ ማለዳ በዚህ ዓመት በጥር ወር የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመመረቂያ ጊዜ ተራዝሞብናል በሚል ትምህርት የማቆም አድማ ማድረጋቸውን መዘገቧ አይዘነጋም። 

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተማሪዎቹ “ይኼን ጊቢ የትምህርት ሚኒስቴር አያውቀውም ወይም ለሚደረግብን ነገር ተባባሪ ነው” ሲሉም ይወቅሳሉ። አዲስ ማለዳ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ለማነጋርገር ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። 

በዲላ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች እንደተናገሩት የምግብ ጥራቱም ጥሩ ባለመሆኑ “ከምንበላበት የማንበላበት ጊዜ ይበልጣል ብዙ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በመግለጫው «ዩኒቨርሲቲው በምግብ እጥረት ምክንያት ተማሪዎችን ሊበትን ነው» እየተባለ የሚሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ በተቋሙ ዘንድ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነውም ብሏል።

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply