የምጥ መርፌ መቼ ይሰጣል?ከ37 እስከ 42 ሳምንታት ባሉት የመጨረሻ የእርግዝና ወራቶች ላይ ምጥ ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ የሚመጣ ይሆናል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግን ምጥ በሚጠበቅበት ጊዜ ላይመ…

የምጥ መርፌ መቼ ይሰጣል?

ከ37 እስከ 42 ሳምንታት ባሉት የመጨረሻ የእርግዝና ወራቶች ላይ ምጥ ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ የሚመጣ ይሆናል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግን ምጥ በሚጠበቅበት ጊዜ ላይመጣ የሚችልበት እድል ይኖራል፡፡

ታዲያ የምጥ ምልክቶች የማይስተዋሉ ከሆነ፤ ነፍሰጡር እናት በተለያዩ የህክምና መንገዶች በሰላም እንድትገላገል የሚደረግ ይሆናል ተብሏል፡፡ ቀዳሚ የሚሆነው የዘገየውን ምጥ የምጥ መርፌን በመውጋት በአርቴፊሻል መንገድ ምጥ እንዲመጣ ማድረግ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የመጨረሻ የወር አበባ ከታየበት ከ9 ወር ከ5 ቀን እስከ 10 ወር ድረስ የሚመጣ ምጥ ጊዜውን የጠበቀ ነው ያሉት፤ የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስ ዶክተር እስክንድር ግዛው ናቸው፡፡

ምጥ ጊዜን ጠብቆ የማይመጣ ከሆነ እና በህክምናው ጽንሱ መቀጠል እንደሌለበት ከታመነ በህክምና የምጥ ማምጫ መድሃኒትን በመጠቀም ነፍሰጡር እናት በሰላም እንድትገላገል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በአብዛኛው ምጥ ጊዜውን ጠብቆ የሚመጣ ቢሆንም፤ ምጥ የሚዘገይበት ምክንያቶች መኖራቸው ተመላክቷል፡

•ከዚህ ቀደም በነበረው እርግዝና ምጥ በጊዜው ካልመጣ
•ወንድ ልጅ ከተረገዘ
•እናት ከእርግዝና በፊት የነበራት ክብደት እና በእርግዝና ወቅት ክብደት ከጨመረች

#የምጥ መርፌ መቼ ይሰጣል?

•የሽንርት ውሃ ፈሶ ምጥ ካልመጣ
•በእናት እና በጽንሱ ላይ የጤና እክል ካለ
•እርግዝናው ከ41 ሳምንታት በላይ ሆኖት የምጥ ምልክቶች የማይስተዋሉ ከሆኑ
•የጽንስ መፋፋት እና የጽንስ ቁጥር ከጨመረ የምጥ መርፌ መጠቀም ሊያስፈልግ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የመጨረሻ የእርግዝና ጊዜያት ሊከብዱ እና አስጨናቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊኖር የሚችል በመሆኑና ስለ ምጥ መርፌ በቂ ግንዛቤ ከሌለ ሁኔታውን ሊያከብደው ስለሚችል፤ ለወሊድ የደረሰች እና የሚያጨንቋትን ጉዳዮች ሀኪሟን በቅርበት መጠየቅ ለአላስፈላጊ ጭንቀት እንዳትዳረግ ይረዳል ተብሏል፡፡

የሽርት ውሃ ቀድሞ የፈሰሳቸው፣ የምጥ መርፌ የተመከሩ እናቶች ከሀኪማቸው ጋር በግልጽ መነጋገር እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡

ለወሊድ የደረሱ እናቶች የምጥ መርፌን መጠቀም ካልፈለጉ ምጥ የሚያመጣው መድሃኒት የማይሰጥበት ሁኔታ መኖሩ ተመላክቷል፡፡ የምጥ መርፌ ለሁሉም የማይሰጥ መሆኑ እና በተለያዩ ምክንያቶችም ላይሳካ የሚችልበት ሁኔት ሊኖር እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የምጥ መርፌ ብዙዎችን ሲያስጨንቅ የሚስተዋል ሲሆን፤ ለወሊድ የደረሱ እናቶች በተሳሳተ መልኩ እንዳይረዱት ይረዳ ዘንድ የምጥ መርፌ ለማን ፣ መቼ እና እንዴት እንደሚሰጥ እንዲሁም ከዛ በኋላ ስለሚኖሩ ሁኔታዎች በተመለከተ በዘርፉ ባለሞያዎች ሰፋ ያለ ግንዛቤ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡

በእሌኒ ግዛቸው

ሰኔ 05 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply