የሟች ቢላል ታዴ አስከሬን ወደ ትውልድ ስፍራው መሸኘቱ ተገለፀ! ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ቡልቡላ ማርያም በተባለ አከባ…

የሟች ቢላል ታዴ አስከሬን ወደ ትውልድ ስፍራው መሸኘቱ ተገለፀ! ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ቡልቡላ ማርያም በተባለ አከባቢ ትናንት ጥር 12/2015 ዓ/ም ከከተማዋ ፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ያለፈው የቢላል ታዴን አስከሬን ስርዓተ ቀብሩን ለመፈፀም ከዘውዲቱ ሆስፒታል ተረክበው ወደ ትውልድ ስፍራው እየወሰዱ መሆናቸውን የሟቹ ቤተሰቦች እና ጓደኞች ለአማራ ድምፅ ገለፁ። የከተማዋ ፀጥታ ኃይሎች ትናንት ጥር 12/2015 ዓ/ም የቅዱስ ሚካኤል ፅላት ከባህረ ጥምቀቱ ወደ መንበሩ ሲመለስ አጅበው ከሚጓዙ አማኞች መካከል የአፄ ቴዎድሮስን ጨምሮ የቀድሞ ነገስታት ምስል ያለበትን ቲሸርት የለበሱ ወጣቶችን መርጠው ለመያዝ ሲሞክሩ በዚህ መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ነው በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ለአማራ ድምፅ የተናገሩት። በዚህም ከፀጥታ ኃይሎቹ በተተኮሰ ጥይት ቢላል ታዴ የተባለ ወጣት ሲገደል ሌሎች አምስት ወጣቶች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸው ተገልጿል። ድርጊቱ የተፈፀመው ትናንት ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ሲሆን ቢላል ታዴ የተባለው ወጣት ከፀጥታ ኃይሎቹ በተተኮሰ ጥይት እንደተመታ በአቅራቢያው በሚገኘው ዋሽንግተን ሆስፒታል ቢወሰድም ነገር ግን ህይወቱ ማለፉን ነው የሟቹ ጓደኞች ለአማራ ድምፅ ያረጋገጡት። አስከሬኑ ለተጨማሪ ምርመራ ከዋሽንግተን ሆስፒታል ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የተላከ ሲሆን የሟቹ ቤተሰቦች አስከሬኑን ወደ ትውልድ ስፍራው እንዳይወስዱ ጫና ሲደረግባቸው መዋሉንም አመላክተዋል። ከብዙ ደጅ ፅናት ቦኋላ አስከሬኑን ከዘውዲቱ ሆስፒታል መቀበላቸውን ለአማራ ድምፅ የገለፁት የሟች ቤተሰቦች እና ጓደኞች፡ስርዓተ ቀብሩን ለመፈፀም ወደ ትውልድ ስፍራው እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣት ቢላል ታዴ ትውልዱና እድገቱ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ሲሆን፡ በአዲስ አበባ ከተማ በታክሲ ረዳትነት ስራ ተሰማርቶ ይኖር እንደነበርም ተገልጿል። የአማራ ድምፅ ያነጋገራቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የቡልቡላ አከባቢ ነዋሪዎች፡በዛሬው እለት በርካታ የአከባቢው ወጣቶች በከተማዋ ፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን ገልፀው፡ ግድያውን የፈፀሙት እነሱ ናቸው በሚል የሀሰት ክስ ሊመሰርቱባቸው ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰተዋል። ዘገባው የአማራ ድምፅ ነው “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply