
የሥርዓቱ ሥርዓት አልበኝነት ገደቡ የት ነው?! በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ ፓርቲዎች የዛሬ ኹለት ዓመት ገደማ በተደረገው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እኛን ጨምሮ ብዙ ፓርቲዎች ውጤቱ ከእኛ አንጻር ብዙ መልካም ነገር ይዞ እንደማይመጣ እያወቅን ስለሀገር መጽናት ሲባልና በነበረው ከባቢያዊና ዓለምአቀፋዊ ጫና ሳቢያ ምርጫው ላይ ብዙ ልብ የሚያሸፍቱ ነገሮች ቢፈጸሙም ከፍ ባለ ጨዋነት በምርጫው በመሳተፍ በታሪክ ተጠቃሽ ሥራ ሠርተናል፡፡ ሆኖም ሥርዓቱ እንዲህ ያለውን ሓላፊነት የተሞላው እንቁ ተግባር ለሀገር ማጽኛ መሠረት ሳይሆን ሕዝብን ለመበደል፣ አኝኮ አኝኮ ወደዘመዱ ለመዋጥ፣ የጦር ድግስ ማጋፈሪያና ቂምና ቁርሾን ለመወጣት የሀገር ዐምዶችን ለመነቅነቅ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ብልጽግና፣ የፌዴራል መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድም ሦስትም ሆነው የዜጎችን መብቶች በመጨፍለቅና ግፍ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ። የግፉ ጽዋ ሞልቶ ከመፍሰሱ በፊት የሥርዓቱን ሥረዓት አልበኝነት ልጓም ይበጅለት እንላለን፡፡ 1. በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በርካታ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖቻችን ጥረው ግረው ከሠሩት መኖሪያ ቤታቸውና ቀያቸው እየተሳደዱ ይገኛሉ፡፡ በውድቅት ሌሊት ቤታቸው በላያቸው ላይ እየፈረሰ ነው፤ ሰዎች እየተደበደቡ፣ በማንነታቸው ከፍተኛ ግፍ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ቢሯችን ድረስ በመምጣት አቤት እያሉ ነው፡፡ ሥርዓቱ በጥደፊያ እያስፈጸመው ያለው የ“ሸገር ከተማ” ፕሮጀክት አዲስ አበባን ጥቅም አልባ የማድረግና ነዋሪውንም የቂም በትሩን ለማሳረፍ እያመቻቸው እንደሚገኝ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ግፍ ወለድ ብሶት እንኳን አደባባይ ወጥቶ እንባውም ጎርፍ ሆኖ እንደሚወስዳችሁ ለአፍታም እንዳትጠራጠሩ፡፡ በመሆኑም ይህ ግፍ በአስቸኳይ ይቁም እንላለን፡፡ 2. የጉራጌ ዞን ማኅበረሰብ ክልል የመሆን ጥያቄውን በሕገ መንግሥቱ ላይ ተመሥርቶ፣ ለሌሎች ባስጀመራችሁበትና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ አቅርቧል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ያለበትን የዋለ ያደረ፣ ጊዜ የማይሰጥ የወሐ ጥያቄ እንዲሁ በጨዋነት አቅርቧል፡፡ ሰሚ አጥቶ ጥሙ ሲበረታበትም ባዶ ጀሪካን ይዞ አደባባይ ወጥቷል፡፡ ሆኖም ብቅ ያለችን ተቃውሞ በአፈሙዝ ለመፍታት የሚታትረው ሥርዓቱ ለጥሙ ምላሽ በሞት ድግስ መልሶለታል፡፡ ዓላማው ማኅበረሰቡን ከኢትዮጵያዊነት ማማ ለማውረድ፣ ቂም መወጣትና ለሌሎች መቀጣጫ ማድረግ ነው፡፡ ስለሆንም የዞኑ ማኅበረሰብ ፍትሓዊና ሰላማዊ ጥያቄ በአግባቡና በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን፡፡ 3. በመስጠት፣ በእንግዳ ተቀባይነትና በቀንድ ከብቶቹ የሚታወቀው ቦረና ምን አልባት በዓመት ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ድርቅ ተመትቷል፡፡ የቀንድ ከብቶቹ እየረገፉ ነው፣ ሰዎችም ከድርቁ ጽናት የተነሳ መሞት መጀመራቸው ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ፈታኝ ወቅቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ተከስተዋል፣ ይከሰታሉ፡፡ ቁምነገሩ ችግሩን ተረድቶ አስፈላጊና ወቅታዊ ምላሽ መስጠቱ ላይ ነው፡፡ የክልሉና ፌዴራል መንግሥት በመናበብ ሀገር አፍራሽ ሽሚያ ውስጥ ከመግባት ይልቅ እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶችን ወደመረዳትና ወደመፍታት ቢያደሉ ኖሮ እንዴት በታደልን፡፡ ስለሆነም ሕዝብና ከብቱ በረሃብ ከማለቃቸው በፊት መላው ኢትዮጵያውያንና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ግዴታውን እንዲወጣ በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡ መንግሥትም በባዶ ሜዳ ፉከራውን አቁሞ ለረጂ ተቋማት ጥሪ እንዲያደረግ እናሳስባለን፡፡ 4. የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች በቅርቡ በነነዌ ጾም ወቅት በቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ “ጥቁር ልበሱ” ተብለው ስለነበር አምነውበት ጥቁር ለብሰዋል። ሆኖም “ለምን ጥቁር ለበሳችሁ?” እየተባሉ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው እየተባረሩ ይገኛሉ። ይህ ተግባር ያለጥርጥር በማን አለብኝነት የሚፈጸም፣ መንግሥት የልብስ ቀለምን መምረጥ ጀመረ ወይ? የሚያስብል፣ የዕምነት ነጻነትን የሚጨፈልቅ ድርጊት ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም በዚሁ ሰበብ ከሥራ ገበታቸው የተባረሩ ዜጎች በአስቸኳይ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አጥብቀን እንጠይቃለን። 5. ከሰሞኑ በአዲስ አበባ አስተዳደር በአውቶቡስ ግዥ ስም የተፈጸመውን ምዝበራ በሚመልከት “ግመል ሠርቆ፣ …” ዓይነትና ሥርዓቱ ከሕግ ማስከበር አቅም አጠርነት፣ እኔ ብቻ ልብላው አደገኛ አካሄድ በተጨማሪ ከባድ ሥርዓት መር ሙስና ውስጥ ለመዘፈቁ ጉልህ ማሳያ አድርገን እንወስደዋለን፡፡ ስለሆነም አግባብ ያለው የሕዝብን ጥያቄ በመደበቅና በማዳፈን ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ የተሠራውን ስህተት በገለልተኛ ኦዲተር ተጣርቶ ለሕዝብ እንዲገለጽ፣ በስህተት ውስጥ የተሳተፉ አካላትም በይፋና በተዋረድ ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ እናሳስባለን፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ መኢአድ፣ እናት እና ኢሕአፓ ፓርቲዎች የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
Source: Link to the Post