
የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በልዩ ድምቀት ተከብሯል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በእያመቱ በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ እንግዶች እና የእምነቱ ተከታዮች የሚሳተፉበት የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል ዘንድሮም በደብረ ታቦር ከተማ በልዩ ድምቀት ተከብሯል። በደብረታቦር ከተማ የሚከበረውን የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓልና በእለቱ ደምቆ የሚውለውን የፈረስ ጉግስን በማስመልከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንግዶቹን በመያዝ ከ1990 በኋላ የተደረገ የመጀመሪያውን በረራ ከአዲስአበባ ቀጥታ ወደ ደብረታቦር ማድረጉን የደብረ ታቦር ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ዘገባ አመልክቷል። የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ታቦት ከመንበሩ ወጥቶ ወደ አጅባር እንዲወሰድ በማድረግም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን፣ ሀይማኖታዊ ስርዓትን፣ አማራዊ ወግ እና ባህሉን በጠበቀ መልኩ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ተደርጓል። አሚኮ እንዳጋራው በክብረ በዓሉ ከተገኙት የክብር እንግዶች መካከል የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ ስለቅርሶቹ የላቀ አስተዋጽኦ፤በማስተዋወቅ፣በማልማትና በማሻገር በትኩረት ሊሠራ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንም ማሳደግ ብሎም የቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ፣በድምቀትም እንዲከበር መስራት ተገቢ ስለመሆኑ ተናግረዋል። በዓሉን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ዓለማቀፍ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማድረግም መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። በተያያዘም የደብረታቦር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው “የደብረ ታቦርን የአጼ ቴዎድሮስ ያልተቋጨ ህልም መግለጥ የዚህ ትውልድ ኀላፊነት ነው” ብለዋል። መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እና የቅርብ ክትትል እንዲያደርግም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Source: Link to the Post