You are currently viewing “የሰሜኑ ጦርነትም እንደገና ለመቀጣጠል በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ቢሆንም መንግስት ልክ ጦርነቱ ያለቀ ይመስል በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተጠምዶ ህዝብን በማዘናጋት ላይ ይገኛል” የመላው ኢት…

“የሰሜኑ ጦርነትም እንደገና ለመቀጣጠል በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ቢሆንም መንግስት ልክ ጦርነቱ ያለቀ ይመስል በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተጠምዶ ህዝብን በማዘናጋት ላይ ይገኛል” የመላው ኢት…

“የሰሜኑ ጦርነትም እንደገና ለመቀጣጠል በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ቢሆንም መንግስት ልክ ጦርነቱ ያለቀ ይመስል በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተጠምዶ ህዝብን በማዘናጋት ላይ ይገኛል” የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ላለፉት 30 ዓመታት ለህዝብ እኩልነትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ብርቱ ትግል ሲያደርግና ሲያታግልም መምጣቱን፤ ባለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መከራ ዓመታትም ከፍ ያለ ዋጋ መክፈሉን አውስቷል፡፡ በብዙ መስዋዕትነት የሚገኘው ድል ግን በተለያዩ ምክንያቶች እየተቀለበሰ መሆኑን ተመልክተናል ብሏል መኢአድ በመግለጫው፡፡ ይሁን እንጅ መንግስትን እየመራ ሀገር የከፋ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ሁሉን ችሎና አቻችሎ እንዲመራ የተሰጠውን እድል በአግባቡ ባለመጠቀም የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ከህዝብ የተሰጠውን የይቅርታ እድል በአግባቡ ባለመረዳት በተሳሳተ መንገድ ወስዶታል ነው ያለው መኢአድ የህዝቡን ችግርም ከድጡ ወደ ማጡ ስለማድረጉ ጠቁሟል። በተለይ ባለፉት 3 ዓመታትም በሁሉም የሀገራችን ክፍል የሕዝባችን ደም እንደ ጎርፍ ስለመፍሰሱና ታይቶ የማይታወቅም ግፍ በህዝብ ላይ ስለመፈጸሙ ጠቅሷል፡፡ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ የጦርና የጦረኝነት እንቅስቃሴዎችን መንግስታዊ የደህንነት መዋቅርን ተጠቅሞ ሳይቃጠል በቅጠል በመግታት በኩልም ከፍተኛ ድክመት ማሳየቱን አውስቷል። የሚደርሰውን መረጃ አይቶ እንዳላየ በማለፍ በሁሉም ቦታዎች የሰው ህይወት ከተቀጠፈና ንብረት ከወደመ በኋላ እንደ ቀብር አስፈፃሚ አስከሬንና ፍርስራሽ ላይ ቆሞ ማልቀስና ማስለቀስ ዋነኛ ሥራው አድርጎት ስለመቆየቱም ጠቁሟል፡፡ ይባስ ብሎም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በመንግስታዊ እንዝህላልነትና በተቀናቃኙ ህወሓት እብሪት ምክንያት ወደማንወጣውና ወደ ቀለጠ የእርስ በእርስ ጦርነት በመገባቱ የአማራና የአፋርን ህዝብ በኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ድቀት ውስጥ እንዲዘፈቅ ስለመደረጉም ገልጧል። “እኛ ጦርነትን አንሻም አናበረታታምም፤ ላለፉት 30 ዓመታትም የሰላማዊ ትግል ላይ የሙጥኝ ያልነውም የሰላማዊ ትግልን ፍሬ ጠንቅቀን ስለምናውቅ ነው እንጂ ጦርኝነቱ ጠፍቶን አይደለም” ብሏል መኢአድ በመግለጫው። ይሁን እንጂ አማራጭ አሳጥተውን በገባንበት ጦርነት ምክንያት በዘመናት የማይተካ የኢኮኖሚ ውድመት፣ ከትውልድ አዕምሮ የማይፋቅ የስብዓዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ውስጥ ከመግባታችንም በላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ነፍሳትን ገብረን ያመጣነውን ድል ወደ ዜሮ የሚመልስና ለዳግም ዋጋ የሚያዘጋጅ የስህተት ውሳኔ አሁንም በመንግስት ተወስኗል ብሏል፡፡ የዚህ ሁሉ የመከራና ሀገርን የማፍረስ ውጥን (እቅድ) ጠንሳሽና ጠማቂ የሆኑ መርዘኛ የሽብር አለቆችን ብዙ ነፍሳት ተገብሮ በህግ ቁጥጥር ሥር ውለው ህዝባችን ከዛሬ ነገ የፍትህ ዜና እሰማለሁ ብሎ ተስፋ ሲያደርግ ሰው በላ ጠላቶቹን ያለ አንዳች ምክንያት በመልቀቅ የሕዝባችንን ቅስም የሚሰብር ድርጊት መንግስት በህዝባችን ላይ ፈፅሟል ሲል ውሳኔውን አውግዟል፡፡ አሁንም ቢሆን የሰሜኑ ጦርነት ካሳለፍነው በባሰ ዋጋ ሊያስከፍለን በሚያስችል መልኩ የአሸባሪው ኃይል እየተዘጋጀና ህዝብንም በገፍ እያሰለጠነ፣ ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ በመሆኑ፣ በመሀል ኢትዮጵያና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሀገራችን ክፍልም የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ ከምንጊዜውም በበለጠ ተጠናክሮ ህዝባችንን ማህበራዊ እረፍት አሳጥቶት በየቀኑ የሰው ህይወት እየተቀጠፈ ስለመሆኑ ገልጧል። መንግስት የዜጎችን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነት ቢሆንም ተደጋጋሚ በመግለጫና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በግል ደብዳቤ በመፃፍ ብናሳውቅም ጉዳዩን ከቁብ ሊቆጥረው የሚችል የመንግስት አካል አልተገኘም ብሏል፡፡ የሰሜኑ ጦርነትም እንደገና ለመቀጣጠል በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ቢሆንም መንግስት ልክ ጦርነቱ ያለቀ ይመስል በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተጠምዶ ህዝብን በማዘናጋት ላይ ይገኛል ሲል ወቅሷል፡፡ መንግስት ጠላትን በመመከት ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ የነበራቸውን የጥምር ኃይሉን አባላት የአማራ ልዩ ኃይልና የአፋር ልዩ ኃይል እንዲሁም ፋኖ ወደየመጡበት የመመለስና የመበተን አዝማሚያ እያሳየ ስለመሆኑ የገለጸው ድርጅቱ ይሄ ደግሞ አሁንም ያለ በቂ ዝግጅት መከረኛውን ህዝባችንን ለዳግም መከራ መዳረግ ይሆናል ሲል አካሄዱን ተቃውሟል፡፡ የብሔራዊ መግባባት ውይይቱንም መንግስት ከስልጣኑ አልፎ በውይይቱ ላይ ማን መሳተፍ እንዳለበትና እንደሌለበት የመወሰን ጣልቃ ገብነት እያሳየ መሆኑንም ያስረዳል ሲል አክሏል፡፡ በመጨረሻም መኢአድ የሚከተሉትን ጥሪዎች አቅርቧል፡- 1ኛ. መንግስት ህዝብን ከስጋት ዋስትና ከማጣት ስሜት የማስወጣት ተግባሩን በአስቸኳይ እንዲያቆምና ህዝብ በሰላም ተረጋግቶ ኑሮውን እንዲመራ የሚያደርግ መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ 2ኛ. መንግስት ህዝብ አደጋ ሊደርስ እንደሆነ ተረድቶ የሚጠቁመውን ጥቆማ በአስቸኳይ ከጥፋቱ ቀድሞ የሕዝብን እልቂት የሚታደግ ተወርዋሪ ሀገር ወዳድ ኃይል እንዲመድብ፣ 3ኛ. መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ያላቀቀ መሆኑን ተረድቶ በቀጠናው እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ እስከውዲያኛው የሚያስቆም ወታደራዊ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድና በቀጠናው ያለውን ህዝባችንን ደህንነት እንዲጠብቅ፣ 4ኛ. መንግስት በምዕራብና በመሀል ኢትዮጵያ ያለውን የኦነግ ሸኔን እንቅስቃሴ የሚገታ የተጠናከረ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ 5ኛ. መንግስት በጥምር ኃይሉ ላይ የያዘውን አቋም ጦርነቱ ካለማብቃቱ አንፃር በደንብ እንዲያጤነው፣ 6ኛ. መንግስት በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ጣልቃ ገብቶ ተቋማትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት አካሄድን አቁሞ የእስረኞችን የመፍታትና የማሰር ጉዳይን ለፍትህ ተቋማቱ እንዲመልስ በአስቸኳይ እንጠይቃለን፡፡ 7ኛ. የብሔራዊ መግባባቱን ጉዳይ ሊመረጥ ላለው ኮሚሽን በገለልተኛነት እንዲተውና ጣልቃ እንዳይገባ እንጠይቃለን፡፡ 8ኛ. ሕዝባችን፡- በጦርነት ምክንያት መንግስት እየፈፀመ ያለው ስህተት እንዳያዘናጋህና ጦርነቱ እንዳላበቃ ተረድተህ ራህን እና ሀገርህን በንቃት እንድትጠብቅ ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ “አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”

Source: Link to the Post

Leave a Reply