የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም ነዋሪዎችን ማፈናቀል መቀጠሉን ኦቻ አስታወቀ

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ከአማራ፣ ከአፋርና ከምዕራብ ትግራይ መፈናቀላቸውን እንደቀጠሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት /ኦቻ/ ትናንት አስታውቋል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በትናንቱ ዕለታዊ መግለጫቸው እንዳሰፈሩት፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኘው ሸዋ ሮቢት ከተማ በዐስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ አፋር ክልል መሰደዳቸውንና ገልፀዋል። በተጨማሪም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከወልዲያና ከላሊበላ መፈናቀላቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ትግራይ ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጥሩ ሰዎች ወደ ወደ ሰሜን እና ምዕራብ ትግራይ ዞን መሰደዳቸውን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ያለው የፀጥታና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ርዳታ ለማድረስ አስቸጋሪ እንዳደረገው የገለፁት የመንግሥታት ድርጅቱ ቃል አቀባይ፤ በደሴ እና በኮምቦልቻ በተደረገው ማጣራት  የጤና ድርጅቶችን ጨምሮ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መዘረፋቸውን አስታውቀዋል። በኮምቦልቻ የእርዳታ እህል ማከማቻ መጋዘን ላይም ከፍተኛ ዘረፋ መካሄዱን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ዱጃሬክ ከህዳር 22 እስከ 28 ባለው ጊዜ የእርዳታ ምግብ፣ ተመጣጣኝ ምግብ፣ ውሃ እና ለፅዳት አገልግሎት የሚረዱ አቅርቦቶችን የጫኑ 44 መኪናዎች በአፋር ክልል አርገው ወደ መቀሌ መግባታቸውን የገለፁ ሲሆን ከሳምንት በፊት በነበረው ጊዜ 157 ምግብ የጫኑ መኪናዎች መግባታቸውን አስታውሰዋል።

ከሐምሌ 26 ጀምሮ በአፋር መስመር በኩል ነዳጅና መድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች ማለፍ እንዳልቻለ የገለፁት ዱጃሬክ በትግራይ የሚገኙ ሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች በተወሰነ አቅምም ቢሆን ህይወት አድር እርዳታ መስጠት መቀጠላቸውን ገልፅዋል። በዚህም መሰረት ከኅዳር 16 እስከ 22 ባለው ጊዜ 43 ሺህ ሰዎች በትግራይ የምግብ እርዳታ እንደተደረገላቸውና ከነዚህ ውስጥ ከ10 ሺሕ በላይ የሚሆኑት አዳዲስ ተፈናቃይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አጋር ድርጅቶቻችን በአማራ እና በአፋር መድረስ በሚችሉባቸው የተወሰኑ አካባቢዎችም እርዳታ ማድረሳችውን ቀጥለዋል ያሉት ዱጃሬክ፣ በአማራ ክልል ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ 947 ሺህ ሰዎች የእርዳታ እህል እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል።

በሦስት ሆስፒታሎችና 19 የጤና ጣቢያዎች ድጋፍ መሰጠት እንደተቻለም ጨምረው ገልፀዋል። በተመሳሳይ በአፋር ባለፈው ሳምንት ለ16 ሺህ ሰዎች የእርዳታ እህል መከፋፈሉን፣ 26 ሺሕ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች ደግሞ የውሃና የንፅህና ቁሳቁስ አቅርቦት መደረጉትን ዱጃሬክ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply