የሰራንበትን ደሞዝ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ በመጠየቃችን ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰብን ነዉ ሲሉ የስልጤ ወረዳ የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በወረዳዉ ጤና ጣቢያ የሚሰሩ ከ35 በመቶ በላይ የጤና ባለሙያዎች ስራ ስለመልቀቃቸዉ እና ቀሪዎቹም የስራ መልቀቂያ ስለማስገባታቸዉም ሰምተናል፡፡

ከጤና ጣቢያዉ ዉጪ ደግሞ በቅበት ከተማ የሚገኘዉ የቅበት ሆስፒታል ሰራተኞችም ግማሹ ስራ መልቀቃቸዉ ነዉ የተሰማዉ፡፡

በወረዳዉ ጤና ጣቢያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ክፍያ በመጠየቃቸዉ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸዉ መሆኑንም ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡

በወረዳዉ ካለፈዉ ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ የተጠራቀመ የ 6 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ያለፈዉ ወር ደሞዝ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተከፈላቸዉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጤና ጣቢያዉ ሰራተኛ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ሰራተኛዉ ጥያቄዉን ሲያቀርብ ከአስተዳደሩም ሆነ ከአመራሩ በግልጽ‹‹ወየዉላችሁ ጠብቋት!መባረር ካልፈለጋችሁ ትንፍሽ እንዳትሉ ›› የሚል ማስፈራሪያ ነዉ እየደረሰዉ ያለዉ ብለዋል፡፡

የትርፍ ሰዓት ክፍያን ስንጠይቅም ‹‹በጀት የለንም›› ነዉ የምንባለዉ ያሉት ባለሙያዉ ፤ ነገርግን ለማጣራት ባደረግነዉ ሂደት ዞኑ ገንዘቡን ለቅቆ ደሞዙ ወረዳዉ ላይ ሲደርስ ወደ ግለሰብ አካዉንት ገቢ እንደሚሆን ደርሰንበታል ብለዉናል፡፡

ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ አንድ ቦታ የሚሰሩ ወደ 5 የጤና ባለሙያዎች ስራ መልቀቃቸዉን አንስተዉ፤ካለዉ ሁኔታ አንጻር ማንም ወደ ቦታዉ መምጣት አይፈልግም ብለዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ያለዉ ችግር መስተካከል የሚችል አይደለም እኛም በጉዳዩ ተስፋ ቆርጠናል ያሉት ባለሙያዉ ፤ነገርግን ድምጻችንን መንግስት እንዲሰማን እና መፍትሄ ካለዉ እንዲሰጠን እንጠይቃለን ብለዉናል፡፡

የቅበት ሆስፒታል ሰራተኞች ከዚህ በፊት የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ጥያቄያቸዉ መልስ ማግኘት ባለመቻሉ ለ2ወራት ያህል ስራ አቁመዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ፡፡

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply