የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ወቅታዊ የፀጥታ ኹኔታን በማስመልከት የተለያዩ ውሳኔዎች አስተላለፈ

ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ”ጥምር ጦራችን በኹሉም ግንባር በሙሉ ብቃትና ወኔ ጠላትን እየመከተ ይገኛል“ ያለ ሲሆን፤ የከተማዋ ማህበረብ በተለያዩ ኹኔታዎች ስጋት ውስጥ እንዳይገባና የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የሚከተሉት ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡

በዚህም መሠረት:-

1. ማንኛውም እግረኛ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

2. ለጸጥታ ሥራ ስምሪት ከተሰጣቸው ተሸከርካሪዎች ውጭ ማንኛውም ተሸከርካሪ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

3. ከጸጥታ መዋቅሩ ውጭ በየትኛውም ሰዓትና ቦታ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

4. ማህበረሰቡን የሚያውኩ የሃሰት አሉባልታዎች ወይም የሃሰት መረጃዎችን ማሰራጨት በጥብቅ የተከለከለ ነው።

5. በከተማችን የሚገኙ ተፈናቃዮች ከተሰጣቸው የመጠለያ ካምፕ ውጭ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

6. ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ማለትም ባንክ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ሆቴል እና መስል የመንግስትና የግል ድርጅቶችን መዝጋት በጥብቅ የተከለከለ ነው።

7. በከተማችን የሚገኙ የመንግስትና የግል ታጣቂዎች መንግስት በሚያሰማራው የፀጥታ ስራ ላይ ተሳታፊ የመሆን ግዴታ አለባቸው።

8. ማንኛውም ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግለሰብ ሆነ ድርጅት የትኛውንም ሚዲያ ተጠቅሞ የሃሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፣ በተለይ ስለጦርነቱ አሉቧል መዘገብ ሆነ መግለጫ መስጠት በጥብቅ የተከለከለ ነው።

9. ማንኛውም የቤት አከራይ ወይም አልጋ ቤቶች ተከራዮቻቸውንና ተጠቃሚዎቻቸውን የመለየትና ማንነታቸውን የሚለይ ህጋዊ መታወቂያ ስለመኖራቸው የማረጋገጥ ግደታ አለባቸው ፡፡ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለፀጥታ መዋቅሩ ጥቆማ የመስጠት ሃላፊነት አለባቸው።

10. ማንኛውም የከተማችን ማህበረሰብ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር የመቀናጀትና የመተባበር ግዴታ አለበት።

ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች በማያከበር ማንኛውም አካል የፀጥታ መዋቅራችን አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በአጽንኦት ያሳውቃል።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት
ነሐሴ 24 ቀን 2014

Source: Link to the Post

Leave a Reply