የሰብዓዊ መብቶችን እንዳያስከብርና መንግስትን እንዳይወነጅል ማስጠነቀቂያና ዛቻ እንደደረሰበት ኢሰመጉ ገለጸ

👉🏿 “ዋጋ ትከፍላላቹ”

ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መጋቢት 28 ቀን 2016 የመንግስት የደኅንነት አባላት “የኢሰመጉ የስራ ኃላፊ ቤት በመሄድ ዛቻ እና ማስፈራራት የፈጸሙ ሲሆን፤ እየተከታተሏቸው እንደሆነና ከሚሰሩት የሰብዓዊ መብት የማስከበር ስራዎች እንዲቆጠቡና መንግስትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመወንጀል እንዲቆጠቡ ካልሆነ ግን ዋጋ እንደሚከፍሉ ዛቻ ደርሶባቸዋል” ሲል ገልጿል።

ኢሰመጉ በጉዳዩ ላይ ከትንናት በስትያ ባወጣው መግለጫ፤ “በኢሰመጉ ላይ መንግስት እየፈጸመ ያለው ከፍተኛ ጥቃትና ጫና አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል” ብሏል።

በዚህም የኢሰመጉ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በተደጋጋሚ በመንግስት የጸጥታና የደኅንነት አካላት በግዳጅ ቢሯቸው ድረስ በመጥራት ጭምር በሚደርስባቸው ጥቃት፣ ሕገ ወጥ እስራት፣ ከፍተኛ ጫና፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ ከማድረጉም ባሻገር ከስራቸው እየለቀቁ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

እንዲሁም ተቋሙ ከተመሰረተ አንስቶ 1989 በሂደቱ አንድ የጉባዔው ሥራ አስፈጻሚ በፌደራል ፖሊስ ጥይት መገደላቸውን ያስታወሰው ኢስመጉ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከህዳር 2015 እስከ መጋቢት 2016 በኃላፊዎችና በሰራተኞች ተፈጽመዋል ያላቸውን ወሳኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ገልጿል።

እነዚህ ልዩ ልዩ ጥቃቶች እና ከፍተኛ ጫናዎች በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እና የሰብዓዊ መብቶች ስራዎች ምን ያህል አስጊ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በግልጽ የሚያሳይ ነውም ብሏል።

ስለሆነም በኢሰመጉ፣ በስራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችና አባላት ላይ በፌደራልና በክልል መንግስታት እንዲሁም በከተማ አስተዳደሮች እና በሌሎች የመንግስት አካላት እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሳስቧል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት “በኢሰመጉ ላይ በመንግስት አማካኝነት እየደረሱ ያሉ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሱ ጥቃቶች እና ከፍተኛ ጫናዎችን በመገንዘብ እነዚህ ጥቃቶች እና ከፍተኛ ጫናዎች እንዲቆሙና ተጠያቂነት እንዲሰፍን” እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት አገር በቀል ድርጅት ሆኖ በ1984 የተመሠረተና በምዝገባ ቁጥር 1146 ከ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ጀምሮ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዳግም ተመዝግቦ በሕጋዊነት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply