የሰዎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ በጎ አስተዋእጾ አድርገዋል የተባሉ አጫጭር ፊልሞች እና ፎቶዎች ተሸላሚ መሆናቸው ተገለጸ፡፡አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀንን ለማሰብ በሚል በሃገራችን በ201…

የሰዎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ በጎ አስተዋእጾ አድርገዋል የተባሉ አጫጭር ፊልሞች እና ፎቶዎች ተሸላሚ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀንን ለማሰብ በሚል በሃገራችን በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የፊልም ፌስቲቫል ዘንድሮም በይፋ ተከፍቷል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለማችን ግጭቶች በሚደረጉባቸው አከባቢዎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመቃወም በሚል የተጀመረው የፊልም ፌስቲባል ዘንድሮም ለሶስተኛ ጊዜ መደረጉን ጀምሯል፡፡

በመዲናችን በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓትም የሰዎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ በጎ አስተዋእጾ አድርገዋል የተባሉ አጫጭር ፊልሞችን እና ፎቶዎች ተሸላሚ መሆናቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲባሉ በኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት ዙሪያ አሳሳቢ ተብለው በተለዩ በሕይወት የመኖር መብት እና የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም የዘንድሮው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በርካታ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና በርካታ አሳዛኝ ክስተቶች የተፈጠረበት በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ተገልጿል፡፡

በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም በተካሄዱት የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ከ15 በላይ እና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጭር እና የተለያዩ የሰብአዊ መብቶችን የሚዳስሱ ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ ቀርበው ነበር ፡፡

በዘንድሮ ግን ከፊልም ሥራዎች በተጨማሪ በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሙያዎች ዕድል ለመስጠት፣ ለማበረታታት እና ለሰብአዊ መብቶች ሥራዎች ድምጽ ለመሆን በማለም የአጫጭር ፊልም እና የፎቶግራፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ማካተት መቻሉን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን ፤ለሰብአዊ መብቶች ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ይህ ኃላፊነት ከመንግስት ፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም ከሲቪክ ማኅበረሰቡ እና ከሚድያው የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ግለሰብ መብቱን እና ግዴታውን በሚገባ ተረድቶ፣ የሌሎች ሰዎችን መብቶች ለማክበር፣ እንዲሁም የሰዎች መብቶች እንዲከበሩ በአቅሙ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅበት ብለዋል።

አክለውም በውድድሩ የተሳተፉ ሁሉ ጊዜያቸውን፣ የፈጠራ ችሎታቸውን እና አቅማቸውን ለሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ድምጽ ለመሆን መምረጣቸው ለሰብአዊ መብቶች ሥራ አጋዥ እና አበረታች መሆኑን አስረድተው ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

የፊልም ፊስቲባሉ ከታኅሣሥ 3 እስከ ታኅሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጪ በአሶሳ፣ በጋምቤላ፣ በሃዋሳ፣ በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በመቀሌ እና በሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ይካሄዳል ተብሏል፡፡

ታህሳስ 1 በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ዝግጅት የአጫጭር ፊልሞች እና የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎችም እንደሚከተለው ይፋ ተደርገዋል።

በፎቶግራፍ ውድድሩ:-
1ኛ. እዮብ ፈንታው – ‘‘ሁለት ዓለም’’ በሚል ርዕስ፣
2ኛ. መዓዛ አያሌው – ‘‘ሰሚ ያጣ ጩኽት’’ በሚል ርዕስ፣ እና
3ኛ. መቅደላዊት አሰፋ – ‘‘ጎጆ’’ በሚል ርዕስ አሸናፊ ሆነዋል።

ጀማሪ ባለሙያዎች በተሳተፉበት አጫጭር ፊልም ዘርፍ ውድድር፤
1ኛ. አዲሱ ደመቀ – ‘‘ስለ ሕይወት’’ በሚል ርዕስ፣
2ኛ. ኪዳኔ ሀብታሙ – ‘‘እምኅልዎት’’ በሚል ርዕስ፣ እና
3ኛ. ማሩፍ እንደራሴ – ‘‘ሃንጋቱ’’ በሚል ርዕስ ያቀረቧቸው አጫጭር ፊልሞች ያሸነፉ ሲሆን፤

ባለሙያዎች በተሳተፉበት አጫጭር ፊልም ዘርፍ ውድድር ደግሞ፤
1ኛ. አህመድ አብዱ – ‘‘ለምን?’’ በሚል ርዕስ
2ኛ. ዓለምእሸት ታደሠ እና ተክላይ ገብረሃና – ‘‘ታቡ’’ በሚል ርዕስ እና
3ኛ. በረከት ተስፋዬ – ‘‘ተስፋ’’ በሚል ርዕስ ያቀረቧቸው አጫጭር ፊልሞች አሸናፊ ሆነዋል።

በመሣይ ገ/መድህን
ታህሳስ 04 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply