የሰዎች ያለአግባብ መታሰር አሳስቦኛል- ኢሰመጉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ከህግ አግባብ ውጭ ዜጎችን ማሰር እንዲቆም ጠየቀ፡፡ ጉባኤው አስቸኳይ ባለው መግለጫው የብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን ጉዳይ ጠቅሶ የተያዙበት መንገድ ህጋዊ አለመሆኑንና ቤተሰቦቻቸውን ለእንግልት መዳረጉን አብራርቷል ጄኔራሉ ከሰው ጋር ቀጠሮ አለኝ ብለው ከቤታቸው እንደወጡ ሳይመለሱ መቅረታቸውንና ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ለማወቅ በርካታ ስፍራዎችን ማዳረሳቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በመጨረሻም ባህርዳር ከተማ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን፣ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው ለግንቦት 22 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰተጣቸው ገልጿል ጉባኤው፡፡ በሌላ በኩል አቶ ናፖሊዮን ገብረእየሱስ ገብሩ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ጀሞ ኮንደሚኒየም ያለፍርድ ቤት ማዘዣ በፀጥታ ሃይሎች ተይዘው መወሰዳቸውን መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡

የአቶ ናፖሊዮን ቤተሰቦች በፍለጋ በርካታ ፖሊስ ጣቢያዎችን ቢያዳርሱም እስካሁን እንዳላገኟቸውና ተቋሙም በደብዳቤ ጠይቆ መረጃ እንዳልተሰጠው ለአርትስ በላከው መግለጫ አብራርቷል፡፡ ጉባኤው በመግለጫው የነ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ፣ አቶ ታዲዮስ ታንቱ፣ ቲና በላይ፣ አቶ አሸናፊ አካሉና መስከረም አበራ እንዲሁም ሌሎችም መታሰራቸውን ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ያሉ ህግን ያልተከተሉ እስራቶች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የፕሬስ ነጻነት መብቶችን አላግባብ የሚገድብ በመሆኑ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እዲወስድ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply