የሱዳን መንግስት ጦር መምዘዙን አቁሞ ከኢትጵያ ጋር በሰላማዊ መንገድ እንዲደራደር የአገሪቱ ምሁራን ጠየቁ፡፡ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት ሱዳዉያን ምሁራን፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በቀ…

የሱዳን መንግስት ጦር መምዘዙን አቁሞ ከኢትጵያ ጋር በሰላማዊ መንገድ እንዲደራደር የአገሪቱ ምሁራን ጠየቁ፡፡

ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት ሱዳዉያን ምሁራን፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በቀላሉ የሚለያዩ ባለመሆናቸዉ መንግስታቸዉ ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጣ ግፊት እንደሚያደርጉም አስታዉቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና የሱዳን ዉጥረት መነሻዉ ምን ይሆን? የሱዳን ህዝብ ፍላጎትስ ምንድነዉ? ስንል ከሱዳናዉያን ምሁራን ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

ዶክተር ኦማር ላሚን አህመድ በሱዳን ዩንቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ናቸዉ፡፡ እርሳቸዉ ዘመናትን ስላስቆጠረዉ ስለ ኢትዮጵያና ሱዳን ቤተሰባዊ ግንኙነት አንስተዉ የድንበር ዉዝግቡ የሁለቱ አገራት ፍላጎት ሳይሆን የቅኝ ዘመን ርዝራዦች ፍላጎትና ሃሳብ ነዉ ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ዉዝግባቸዉን በአፈ ሙዝ ሳይሆን የሁለቱን አገራት ህዝብ በማቀራረብ የዲፕሎማሲ ስራን በመስራት ነዉ የሚሉት ሱዳናዊ ምሁር፤ ለዚህም የሁለቱ አገራት መሪዎች የህዝቡን ፍላጎት ማዳመጥ አለባቸዉ ነዉ ያሉት፡፡

ከድንበር ዉዝግቡ ባለፈ ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያልተገባ ጥያቄ እንደምተነሳ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ግድቡ የሁለቱ አገራት መጨቃጨቂያ መሆን ነበረበት ስንል ዶክተር ኦማር ላሚንን የጠየቅን ሲሆን፤ ሁለቱም አገራት በቂ ዉሃ አላቸዉ፤ ግድቡ የልማት እንጅ የልዩነት አጀንዳ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡

ሌላኛዉ የሱዳን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዉ ፕሮፌሰር አብዱ ኦስማን በበኩላቸዉ፣ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጦር እንዲማዘዙ እንቅልፋቸዉን አጥተዉ ትርፋቸዉን ለማጋበስ የሚጠባበቁ ሃይሎች ስለመኖራቸዉ አንስተዉ፤ በዚህም ሁለቱ አገራት የእነዚህ መጠቀሚ መሳሪያ እንዳይሆኑ ብልህ ሊሆኑ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡

መንግስት ለመንግስት ከሚደረገዉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተጨማሪ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ ያሳሰቡት ሱዳናዊ ፕሮፌሰር አብዶ ኦማር፣ ለዚህ ደግሞ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በቀላሉ የሚለያዩ አይደሉም የሚሉት እነዚህ የሱዳን ዩንቨርሲቲ ምሁራን፤ ይልቁንም ሁለቱ አገራት ጦር እንዲማዘዙ አሰፍስፈዉ የሚጠባበቁ ሃይሎችን ምኞት በጋራ ማምከን ይገባል ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡም ሆነ የድንበር ጥያቄዉ በሃይል የሚመለስ አይደለም ያሉት ምሁራኑ፣ የሱዳን ህዝብ ከኢዮትጵያ ወገኑ ጋር ወደ ግጭት መግባት አይፈልግም፤ ስለዚህ የሱዳን ባለስልጣናት በሌሎች ሃይሎች መገፋታቸዉን ትተዉ የህዝባቸዉን ስሜት እንዲያዳምጡ ግፊት እንደሚያደርጉም አስታዉቀዋል፡፡

በአባቱ መረቀ

ጳጉሜ 03 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply