የሱዳን ሠራዊት በኢትዮጵያ በኩል ያሉ የድንበር አካባቢዎችን በከባድ መሳሪያ መደብደቡን የአካባቢው ባለሥልጣንና ነዋሪዎች ገለጹ

ተፈጸመ በተባለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል

ዕረቡ ሰኔ 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሱዳን ሠራዊት በኢትዮጵያ በኩል ያሉ የድንበር አካባቢዎችን በከባድ መሳሪያ መደብደቡን የአካባቢው ባለሥልጣንና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በሱዳን ሠራዊት እና በአካባቢው ባሉ ሚሊሻዎች መካከል በተከሰተው ግጭት ሱዳን ሰባት ወታደሮቿ እንደተገደሉባት በመግለጽ በኢትዮጵያ ላይ ክስ መሰንዘሯ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በበኩሉ፤ የሱዳን ምርኮኞችን በአደባባይ ገድሏል በሚል ከሱዳን የቀረበበትን ክስ ውድቅ በማድረግ፣ ሠራዊቱ ግጭቱ በተከሰተበት ስፍራ እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ የገባው የሱዳን ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር መጋጨቱን ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ የሱዳን ጦር በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በመድፍ፣ በሞርታር እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ለቀናት የዘለቀ ድብደባ መፈጸማቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ ደሳለኝ አያና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነዋሪዎችም በተለይ ሰኞ ዕለት የተፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ጠንካራ እንደነበር ተናግረው፤ ማክሰኞ ዕለትም እስከ ከሰዓት በኋላ ጥቃቱ መቀጠሉን ገልፀው፤ ተደጋጋሚ ተኩስና ፍንዳታ መስማት ከጀመሩ ሦስት ቀን እንደሆናቸው አመልክተዋል።

ከሱዳን ጋር በሚዋሰነውና ግጭቱ ያጋጠመበት ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ደሳለኝ አያና እንደተናገሩት፣ የሱዳን ወታደሮች ከዚህ ቀደም በኃይል ከያዟቸው አካባቢዎች ባሻገር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በገቡበት ጊዜ ከወረዳው ሚሊሻዎች ጋር መታኮሳቸውንና ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

ደሳለኝ እንደሚሉት መንግሥት የድንበር ችግሩ በንግግር ይፈታል ያለውና የሱዳን ኃይሎች ባለፈው ዓመት በኃይል ገፍተው የያዙት 30 ሺህ ሄክታር መሬትን አልፈው በገቡበት ጊዜ ነው ግጭት የተፈጠረው።

ጨምረውም፤ በግጭቱ እሳቸው የሱዳን ወታደሮችን እየመሩ የመጡ ናቸው ያሏቸውን አራት “የህወሓት ተላላኪዎችን” ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውንና ከሚሊሻው በኩል ደግሞ አንድ ሰው መሞቱንና የቆሰሉም እንዳሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት በሱዳን በኩል ለተሰነዘረው ክስ በሰጠው ምላሽ፣ ግጭቱ የተከሰተው በህወሓት ድጋፍ የኢትዮጵያን ድንበርን አልፈው በገቡ የሱዳን መደበኛ ወታደሮች መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያና በሱዳን የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱበት በነበረው የድንበር አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት በኹለቱም ወገኖች በኩል ባሉ ታጣቂዎች አማካይነት አልፎ አልፎ ግጭት ሲያጋጥም የነበረ ሲሆን፤ የአሁኑ ግን ለቀናት የዘለቀ ፍጥጫን አስከትሏል።

ነዋሪዎችም የተፈጠረው ግጭት ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ሲሆን፤ አንዳንዶችም በአቅራቢያ ወዳሉ አካባቢዎች የመሄድ ሃሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ባለፉት ሦስት ቀናት ተፈጸመ በተባለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን የተናገሩት የምዕራብ አርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ ደሳለኝ አያና፣ የከባድ መሳሪያዎቹ በእርሻ ቦታዎችና የግብርና ካምፖች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በጥቃቱ ምክንያት በነዋሪው ላይ በተፈጠረው ስጋት ሳቢያ፤ ባለፉት ቀናት በእርሻ ማሳቸው ላይ የተለመደውን የዕለት ከዕለት ሥራቸውን ከማከናወን ተቆጥበዋል ብለዋል።

የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ በርካታ የድንበር ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ በአካባቢው ያለው የንግድና የሥራ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን የገለጹት ነዋሪዎች፤ ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚገናኙበት የድንበር ከተማ የሆነችው የገለባት መተላለፊያ መዘጋቱንም የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሱዳን ክስን ተከትሎ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በኹለቱ አገራት ወታደሮች መካከል ከሰኞ ወዲህ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ሲዘግቡ የቆዩ ቢሆንም፣ ደሳለኝ ግን በአካባቢው ጦርነት እንዳልተካሄደ በመግለጽ ያለው ሁኔታ ከሱዳን በኩል የሚፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት መሆኑን ተናግረዋል።

የሱዳን ጦር ኃይሎች ቃል አቀባይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጦር ሠራዊቱ እየተጠቀሰ የሱዳን ኃይሎች ወደ ደንበር መንቀሳቀሳቸውንና ከአል ፋሽካ አካባቢ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስለመማረካቸው የሚወጡትን ዜናዎች ትክክል እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

የሱዳን የሽግግር ሉዐላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን ግጭቱን ተከትሎ ባለፈው ሰኞ ምሥራቃዊውን የአገሪቱን ክፍል በመጎብኘት ከነዋሪዎች እና ከሠራዊቱ ጋር መገናኘታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ወታደሮች አወዛጋቢ ቦታዎችን በኃይል ተቆጣጥረው የያዙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ሱዳን ወታደሮቿን እንድታስወጣ እና ውይይት እንዲደረግ ስትጠይቅ ቆይታለች።

የአካባቢው አስተዳዳሪ እንደሚሉት በኹለቱ አገራት መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት 10 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ በቁጥጥራቸው ውስጥ ያስገቡት ግን ወደ 30 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከሱዳን ጋር በቅርበት የሚዋሰነው የምዕራብ አርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ ደሳለኝ አያና ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የሱዳን ኃይሎች ስናር፣ ገላሉባን፣ ጎረደም፣ ታች እና ላይ አቦጠር እንዲሁም ሰላም በር የተባሉትን ቦታዎችን በቁጥጥር ሥር አድርገው ቆይተዋል።

ሰፊና ለም በሆነው አወዛጋቢው አካባቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የነበሩ ሲሆን፣ የሱዳን ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ወታደሮቿን ከያዙት ቦታ እንድታስወጣና ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው ድርድር እንዲቀጥልና መፍትሔ እንዲያገኝ ሲጠይቅ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለዓመታት የቆየ የድንበር ኮሚሽን አቋቁመው የይገባኛል ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ሲወያዩ ቢቆይም ከመፍትሔ ሳይደርሱ ቆይተዋል።

ሱዳን ሠራዊቷን ከተያዙት ቦታዎች እንደማታስወጣ ያሳወቀች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳን እርምጃ ወረራ መሆኑን በመግለጽ ድርድር ከመደረጉ በፊት ቦታው እንዲለቀቅ ጠይቃለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply