“የሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት መመሪያን በማይተገብሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል“:-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

ሚኒስቴሩ የአዲስ አበባና የክልል ከተሞችን ጊዜያዊ የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ይፋ አድርጓል

ዕረቡ ሐምሌ 20 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያን በማይተገብሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት መመሪያ ቁጥር 908/2014 ከሐምሌ 05/2014 ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም፤ ከሥርጭት ትሥሥርና ከመሸጫ ዋጋ ጋር ተያይዞ ለተጠቃሚው እየደረሰ አለመሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በተደረገ ክትትልም ሲሚንቶ ከተቀመጠው የሥርጭት መመሪያ ውጪ ከፋብሪካዎች እየወጣ በተለያዩ መጋዘኖችና የሽያጭ ቦታዎች እንደሚገኝ መረጋገጡንም ገልጿል፡፡

በመሆኑም በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከተው የፀጥታ ተቋም ጋር በመቀናጀትና የሲሚንቶ ግብይት ቁጥጥር ቡድን በማሰማራት፤ ከመመሪያ ውጪ እየተከናወነ የሚገኘውን ህገ-ወጥ የሲሚንቶ ግብይት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በአስቸኳይ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ተጠቃሚው የሲሚንቶ ምርት ማግኘት እንዲችል፤ ለሥርጭቱ የተመረጡ አካላት በአስቸኳይ ምርቱን ከፋብሪካ በመቀበል በተላለፈው ጊዜያዊ የመሸጫ ዋጋ እንዲቀርብ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጠይቋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአዲስ አበባና የክልል ከተሞችን ጊዜያዊ የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ የመሸጫ ዋጋ ዝርዝሩ ከሥር ተያይዟል።

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply