የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር እና የጸጥታ ሁኔታ ተግዳሮት ሆኖብኛል አለ፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዉስጥ የሚገኙት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸዉ እንዳያመርቱ የአቅርቦት ሰንሰለቱ በህገወጥ ነጋዴዎች በመጠለፉ ችግር ሆኖብኛል ሲል ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቂ ባለሃብቶች ተንቀሳቅሰዉ ወደ ስራ እንዳይገቡ የጸጥታዉ ሁኔታ ሌላዉ ችግር ነዉ ተብሏል፡፡

አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ ለመሄድ ያለዉ የጸጥታ ሁኔታ አስጊ መሆን ዝዉዉሩ በቂ እንዳይሆን አድርጎታል ነዉ የተባለዉ፡፡

ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጴጥሮስ ማርቆስ፤ህገወጥነትን ለመከላከል እየተሰራ ቢሆንም በቂ አይደለም አሁንም ችግሩ አለ ብለዉናል፡፡

አቶ ጴጥሮስ ሌላዉ ያነሱት ጉዳይ የምንዛሪ አቅርቦት ችግር እና የብድር ሂደቱ የተንዛዛ መሆን አዲስ ለሚገቡ ባለሃብቶች ሁኔታዉን ከባድ እንዳደረገዉ ነዉ፡፡

የብድር አቅርቦት ላይ ያለዉ ችግር በልማት ባንክ በኩል መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነዉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እራሱን የቻለ ልዩ ድጋፍ ማድረግ የሚያስፈልገዉ ነዉ ብለዋል፡፡

የደህንነት እና የጸጥታዉ ችግርም መንግስት ሊፈታዉ የሚገባዉ ስለመሆኑ ነዉ ያነሱት፡፡

በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸዉ መስራት ካልቻሉ የስራ ዕድል አይፈጠርም ፤የዉጪ ምንዛሪም በተፈለገዉ ልክ አይገኝም ያሉት አቶ ጴጥሮስ፤ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚመለከተዉ የመንግስት አካል አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠዉ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply