የሶማሊያ ጦር 50 የአልሻባብ ታጣቂዎችን መግደሉን አስታወቀ

https://gdb.voanews.com/7B07E07E-E1B5-4B7D-A82C-08117FF60100_w800_h450.jpg

የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር በአካባቢው ሲቪሎች በመታገዝ በመካከለኛው ሸበሌ ክልል በሚገኘው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ላይ የታቀደ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዶ ቢያንስ 50 የአልሸባብ ታጣቂዎችን መግደሉን የሶማሊያ ወታደራዊ ኃይል አስታወቀ። 

ብሄራዊ የጦር አዛዡ ቅዳሜ እለት ባወጣው መግለጫ ጦሩ በታጣቂዎቹ ላይ ያካሄደው የታቀደ ዘመቻ የተደረገው መካከለኛው ሸበሌ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ዳሩል-ኒሲም መንደር ውስጥ ነው ብሏል። 

ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በስተሰሜን 217 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው በቅርቡ ከታጣቂዎች ነፃ የወጣችው አዳን ያባል ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው መንደር ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴው እየጨምረ መምጣቱ ተዘግቧል። 

ወታደራዊ ዘመቻው የተካሄደው የሶማሊያ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር አብዲራህማን ዩሱፍ ኦማር አላዳላ የጦር ኃይሉ በዚሁ ግዛት በ48 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 88 የአልሻባብ ተዋጊዎችን ገድሏል ካሉ ከአንድ ቀን በኃላ ነው። 

የሶማሊያ ወታደራዊ ኃይል በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙትን ጋልሙዱግ እና ሂርሻቤሌ ከታጣቂው ቡድን ያስመለሰ ሲሆን፣ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ በድጋሚ የተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ በአልሻባብ ላይ ሁለገብ ጦርነት ማወጃቸው ይታወሳል። 

Source: Link to the Post

Leave a Reply