የሸዋሮቢት ከተማ የመንግሥት የሥራ አመራሮች ወደ ደብረብርሃን እና አዲሰ አበባ ሸሽተዋል ተባለ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር አብዛኛው የመንግሥት የሥራ አመራሮች ወደ ደብረ ብርሃንና አዲስ አበባ መሸሻቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ ሌሎችም የጸጥታ ተቋማት አመራሮች ከተማውን ለቀው ወደ ደብረብርሃንና አዲስ አበባ ከተሞች መሄዳቸው ነው የተነገረው።

አመራሮቹ ከተማዋን ለቀው መውጣት የጀመሩት በዋናንት ሰኔ 27/2015 የከተማዋ ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አብዱ ሁሴን ባለታወቁ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪዎች የቀበሌ መታወቂያ ማውጣትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሲሄዱ፤ የሥራ ኃላፊዎች ባለመኖራቸው አገልግሎት ሳያገኙ እንደሚመለሱ ነው የገለጹት።

ነዋሪዎቹ አክለውም፤ “በከተማው ከተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ውጭ የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ሳይቀር የሉም፡፡ አብዛኞቹ የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ሸሽተዋል፤ ያልሸሹትም በየቤታቸው ተቀምጠዋል።” ሲሉ ተናግረዋል።

“በከተማዋ እና  ዙሪያው ጥይት ሲተኮስ ምንድነው ብሎ የሚጠይቅ ፖሊስ የለም፤ የሚዳኝ አካልም የለም።” ያሉት ነዋሪዎች፤ ነዋሪው የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር በራሱ ጥረት እያደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከተማዋ የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቢኖሩም ራሳቸውን ከመጠበቅ ውጭ የከተማዋን የተሟላ ጸጥታ ማስጠበቅ አልቻሉም ሲሉም ተደምጠዋል።

ባለፈው እሁድ ዕለት ምሽት ከከተማው መውጫ አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች አንድ የሚሊሻ አባል መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይ የሸዋሮቢት ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አብዱ ሁሴን ከተገደሉ ወዲህ ኹለት የሚሊሻ አባላት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ኹሉንም የጸጥታ አካላት ስጋት ውስጥ ማስገባቱ ነው የተገለጸው፡፡

ይህም አብዛኞቹ የጸጥታ ኃይል አባላት ሥራቸውን ትተው እንዲሸሹና በየቤታቸው እንዲቀመጡ አስገድዷቸዋል ተብሏል።

መንግሥት “የአማራ ክልል መንግሥትን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቁስ ጽንፈኛ ኃይሎች አሉ” በማለት የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን ካሳወቀ ወዲህ፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ሥራ አመራሮች እና የጸጥታ ኃይል አባላት ላይ ግድያ ሲፈጸም ይስተዋላል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply