የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከእስር መፈታታቸው ተሰማ

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከእስር መፈታታቸው ተሰማ

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከእስር መፈታታቸው ተሰማ፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉትና እስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር፤ ከእስር የተለቀቁት ዐቃቤ ሕግ ክሱን በማንሳቱ መሆኑን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ  እስክንድር ገዛኸኝ እንደተናገሩት፤ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክሳቸው ተነስቶ የተለቀቁት በዛሬው ዕለት  መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል።

ከአቶ አብዲ በተጨማሪም በተመሳሳይ በእሳቸው የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ የሌሎችም ተከሳሾች ክስ ተቋርጦ መለቀቃቸውን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪው እንደሚሉት፣ ዐቃቤ ሕግ ባለው ሥልጣን መሠረት የክስ ማቋረጫውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ፣ አቶ አብዲ ከመፈታታቸው ውጪ ለጊዜው የደረሳቸው ዝርዝር ማብራሪያ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“አሁን ማረጋገጥ የምችለው አቶ አብዲ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ከማረሚያ ቤት መፈታታቸውን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ስላቀረበው ጥያቄ የደረሰን ነገር የለም” ሲሉ  የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከእስር መውጣታቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሲመሩ የነበሩት አቶ አብዲ፣ በክልሉ ውስጥ ከተፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ግድያዎችና የመንግሥት ሀብት ብክነት ጋር ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል።
 
በቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከልም በ2010 ሰኔ እና ሐምሌ ወራት ውስጥ “በሶማሌ ክልል የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ በማሰብ ‘ሄጎ’ በሚል ስያሜ የሚታወቅ ወጣቶች ቡድን አደራጅተዋል” የሚል ይገኝበታል።

በወቅቱ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው፣ እንዲሁም ንብረትና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply