You are currently viewing የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ የፌደራል ሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነታቸውን ዛሬ ሊረከቡ ነው

የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ የፌደራል ሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነታቸውን ዛሬ ሊረከቡ ነው

በሃሚድ አወል

የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ የፌደራል ሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነታቸውን ዛሬ ሊረከቡ ነው። ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪነታቸው ከተነሱ በኋላ አስር ወራትን በእስር ያሳለፉት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ የፌደራል የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎትን በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነው።

አቶ ዳጋቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፈረሙበትን የሹመት ደብዳቤ ትላንት ሐሙስ ታህሳስ 20፤ 2015 ከሰዓት በኋላ መቀበላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”  የተመለከተችው እና ለአዲሱ መስሪያ ቤታቸው በግልባጭ እንዲደርስ የተደረገው ደብዳቤ አቶ ዳጋቶ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 19፤ 2015 ጀምሮ መሾማቸውን ይገልጻል፡፡

ከየካቲት 2012 ጀምሮ የፌደራል ሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ሙሉቀን አማረ እና አዲሱ ተሿሚ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ዛሬ ታህሳስ 21፤ 2015 ርክክብ እንደሚያደርጉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

አቶ ዳጋቶ ከ2011 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ገደማ የወላይታ ዞን አስታዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሩቁ ዳጋቶ ከሁለት ዓመት ከአምስት ወር በፊት ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪነታቸው ተነስተው በቁጥጥር ስር ውለው ነበር፡፡ አቶ ዳጋቶ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከሌሎች ዞኑ አመራሮች ጋር በጋራ በህዳር 2013 በሶስት መዝገቦች ሶስት የተለያዩ ክሶች በደቡብ ክልል ዐቃቤ ህግ ተመስርቶባቸው ነበር።

በወቅቱ ከሌሎች የዞኑ አመራሮች ጋር በደቡብ ክልል ዐቃቤ ህግ የቀረበው የመጀመሪያው ክስ “ስልጣናቸውን አላግባብ የመገልገል” ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው። ከአቶ ዳጋቶ ጋር በተመሳሳይ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ በነበሩት አቶ ጎበዜ ጎዳና እና የወላይታ ዞን የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተከተል ጎአ ይኼው ክስ ቀርቦባቸው ነበር። የደቡብ ክልል ዐቃቤ ህግ አቶ ዳጋቶ ላይ ያቀረበው ሁለተኛው ክስ ደግሞ  ከነብይ ኢዩ ጩፋ የጉቦ ገንዘብ በመቀበል የኢንቨስትመንት መሬት እንዲሰጣቸው አድርገዋል የሚል ነበር።

የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮችን ጉዳይ ሲመከለከት የነበረው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ ወንጀሉን ባለመፈጸማቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን የሰጠው በ2013 መጨረሻ ላይ ነበር። ፍርድ ቤቱ አቶ ዳጋቶን ጨምሮ የወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮች በነጻ እንዲሰናበቱ የበየነው “የቀረበባቸውን ወንጀል በሚገባ ተከላክለዋል” በሚል ነው። ሶስተኛው ክስ እና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭ አካባቢ ተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት ሲቀርብ የነበረው ደግሞ “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት በኃይል የመናድ ወንጀል” ፈጽማችኋል የሚል ነው። አቶ ዳጋቶ በሁለቱ የመጀመሪያ ክሶች ነጻ ከተባሉ ከአንድ ዓመት በኋላ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በተመሳሳይ በሶስተኛውም ክስ ነጻ ተብለዋል።

አቶ ዳጋቶ በመጨረሻው እና ሶስተኛው ክስ ነጻ እስከ ተባሉበት ሰኔ 2014 ድረስ  ለአንድ ዓመት ያለምንም ስራ መቀመጣቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሶስተኛው ክስ ነጻ ከተባሉ በኋላ በደቡብ ክልል የፍትህ አካላት ስልጠና እና የህግ ምርምር ማዕከል ውስጥ በአሰልጣኝነት ተመድበው ሲሰሩ ቆይተዋል።

ከወረዳ ፍትህ ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊነት የሰሩት አቶ ዳጋቶ ከወላይታ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱ የቀድሞ አመራሮች አንዱ ናቸው። የዞኑ አስተዳዳሪ በነበሩት ጊዜ የወላይታ ዞን ተወካዮች የደቡብ ክልል ምክር  ቤት በጠራው ስብሰባ ላይ ላለመሳተፍ አድማ መትተው ነበር። ተወካዮች ስብሰባውን ላለመሳተፍ የወሰኑት የዞኑ ህዝብ ለምክር ቤቱ ያቀረበው በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ “ተደማጭነት አላገኘም” በሚል ነበር።

አቶ ዳጋቶ ከዞን አስተዳዳሪነት ከመሳታቸው ሁለት ወራት አስቀድሞ የዞኑ ምክር ቤት የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ምክር ቤቱ በወቅቱ የክልሉን መንግስት ለማደራጀት የሚያስችል ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም እንዲከናወኑ ወስኖ ነበር።

የዞኑ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ካሳለፈ ሁለት ወራት ገደማ በኋላ ደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ አቶ ዳጋቶን ጨምሮ የዞኑ አመራሮች ከኃላፊነታቸው አንስቷል።  በሰብዓዊ መብት እና በወንጀል ፍትህ አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው አቶ ዳጋቶ ከህዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ  እስከ ነሐሴ አጋማሽ 2012 ዓ.ም ድረስ ዞኑን አስተዳድረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ የፌደራል ሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነታቸውን ዛሬ ሊረከቡ ነው appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply