የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ታዬ ደንድአ የቀረበባቸው ክስ እንዲሻሻልላቸው ያቀርቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ታዬ ደንድአ “ክሱ ይሻሻልልኝ” በሚል ያቀረቡትን ጥያቄ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ችሎት ዛሬ በዋለው ቀጠሮ ውድቅ አድርጎታል።

እንዲሁም የዕምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታው “የጻፍኩት ጽሁፍ ፕሮፖጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም” ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያመለክታል።

ታዬ ደንድአ ከታህሳስ 1 ቀን 2016 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ በተጻፈላቸው ባለሦስት መስመር የስንብት ደብዳቤ ላይ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው ከኅላፊነታቸው መነሳታቸው እንደተገለጸ አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

በመቀጠልም “የሰላም ሚንስትር ዲኤታ ሆነው ሰላምን ለማስፈን መሥራት ሲገባቸው፤ በተቃራኒዉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር” በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸው አይዘነጋም።

በዛሬው ዕለት የዋለው ችሎት ጥያቄውን መርምሮ ክሱን ለማሻሻል የሚያስችል የሕግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

በአንጻሩ ታዬ ዐቃቤ ሕግ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ብቻ ብሎ በክሱ መጥቀሱን ገልጸው፤ “የኦሮሚያ ምክር ቤት አባልና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነኝ በማለት ይኽም ተካቶ ይስተካከልልኝ” ማለታቸው ተገልጿል።

እንዲሁም ረቂቅ ጽሁፍ፣ ሁለት ሞባይሎች እና አንድ ታብሌት ተይዞብኛል፤ ይመለስልኝ ሲሉ አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በአቤቱታቸው ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ታዬ ደንድአ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ጨፌ ኦሮሚያ ባካሄደው 6ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ያለመከሰስ መብታቸውን አንስቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply