የቀድሞ ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ እና የኢጋዱ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እንዲሁም ሌሎችም በድጋሚ በአካል ፍርድ ቤት ቀርበው መከላከያ ምስክርነታቸው እንዲሰማ ታዘዘ

ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የቀድሞ ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ እና የኢጋዱ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎችም በሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው የመርከብ ግዢ እና እርሻ መሳሪያ ክስ ላይ የመከላከያ ምስክርነታቸው በአካል ቀርበው እንዲያሰሙ በድጋሚ ታዘዘ።

ቀደም ሲል በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ እንዲመሰክሩ ታዞ የነበረው ትዕዛዝ ተቀይሮ ነው፤ በአካል ቀርበው እንዲመሰክሩ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሚሰሰና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ያዘዘው።

ከኹለት ወር በፊት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው የእርሻ መሳሪያና የመርከብ ግዢ ሙስና ክስ ላይ በተቆጠሩበት የመከላከያ ምስክርነት በተደጋጋሚ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰቶ ባለመቅረባቸው ምክንያት ታስረው እንዲቀርቡ መታዘዙ ይታወሳል።

”መጥሪያ ሳይደርሰኝ ታስሬ እንድቀርብ የተሰጠው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተገቢ አደለም” ሲሉ ከኢትዮጵያ ውጪ እንደሚገኙና የሥራ ጫና እንዳለባቸው አመላክተው በአካል ለመቅረብ እንደሚቸገሩ በመግለጽ ባሉበት ቦታ የምስክርነት አሰማሙ ቨርቹዋል ቴክኖሎጂ እንዲሆንላቸው ጠይቀው ነበር።

በዚህ ጥያቄያቸው ላይ ከከሳሽ ዓቃቢህግም ከሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጠበቃ ሀፍቶም ከሰተ በኩል መቃወሚያ አልቀረበም።

ፍርድ ቤቱም የሀይለማርያም ደሳለኝ ቋሚ ምስክርነትን ለመስማት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የት አገር፣ የት ቦታ በምን ሰዓት እንደሚገኙ የተከሳሽ ጠበቃ በዝርዝር በጽሁፍ ገልፀው እንዲያቀርቡ አዝዞ ነበር።

በዚህ ትዕዛዝ መሰረት ጠበቃ ሀፍቶም ከሰተ የሀይለማርያም ደሳለኝ ቋሚ መኖሪያ አ/አ ከተማ መሆኑና ነገር ግን፤ ትክክለኛ አድራሻ ኖሯቸው እዚህ ቦታ ይገኛሉ ብሎ መግለፅ የማይቻል መሆኑን ጠቅሶ፤ ወደ ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜያት የሚመላለሱ መሆናቸውን በመገናኛ ብዙሃን ከሚሰራጩ መረጃዎች የተረዳ መሆኑን በመግለጽ በአንድ ገጽ ምላሽ በሰኔ 21 ቀን 2014 አሳውቋል።

እንዲሁም ጠበቃው ተወካያቸው ሀይለማርያም ወደ አገር ውስጥ የሚመጡበትን አጋጣሚ ካለ እንደሚያሳውቋቸውና በማመጡበት ጊዜ በአካል ቀርበው ችሎት እንዲመሰክሩ ይህ የማይቻልበት ሁኔታ ካለ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ሰዓት ካለ ባላቸው አገሮች በሚሆኑበት ሰዓት በተወካያቸው በኩል ለፍርድ ቤት እንዲያሳውቁ እንዲታዘዝለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም ሀይለማርያም በውጭ አገር በተወሰነ ጊዜ ብቻ ከቆዩ በኋላ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ስለሚቀሳቀሱ በዚህ ጊዜ የኔትወርክ ተደራሽነት የሌለ መሆኑን እና ከኢትዮጵያ መደበኛ ሰዓት የሥራ ሰዓት አቆጣጠር ጋር የማይጣጣም የማይገጥም ሁኔታ በመኖሩ እና የምስክር አሰማሙ ሂደቱ የሚያሳልጥ እንዲሁም በህጉ መሰረት ሥርዓትና ቁጥጥር ተጠብቆ ሊሰማ የማይችልበት አስቻይ ሁኔታ ያለመኖሩን ተገንዝቧል።

ለምስክር አሰማሙ ሂደቱ የተሻለ አማራጭ የሚሆነው እና ፍትህን ለማቀላጠፍ የሚጠቅመው ሀይለማርያም በአካል ቀርበው መሰማት በመሆኑ እስከ ሀምሌ 30 ቀን 2014 ድረስ ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡባቸው ማንኛውም ጊዜያት በህጋዊ ወኪላቸው ወይም በጠበቃ በኩል ለችሎቱ ከ48 ሰዓት በፊት በማሳወቅ ቀርበው ምስክርነታቸው እንዲሰሙ ሲል ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በተመሳሳይ መልኩ በሩዋንዳ ኪጋሊ ይገኛሉ የተባሉት ካውንስለር ካሳ ገ/ዩሐንስ፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ ይገኛሉ የተባሉት አንባሳደር ፍስሐ አስገዶም እንዲሁም በአሁን ወቅት በሩዋንዳ ሉሳካ ይገኛሉ የተባሉት የአውሮታ ህብረት አንባሳደር ጄሴክ ጆንዊስኪ በፖስታ ቤት መጥሪያ ደርሷቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ ከሀምሌ 25 እስከ ሀምሌ 29 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል፤ በመርከብ ግዢ የሙስና ክስን በተመለከተ የኢጋዱ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከሀምሌ 11 ቀን እስከ ሀምሌ 13 ቀን በአ/አ በሚገኘው የኢጋድ ጽ/ቤት መጥሪያ ደርሷቸው በአካል ቀርበው እንዲመስክሩ ታዟል።

በተጨማሪም በመከላከያ እጅ ይገኛሉ የተባሉት ሌ/ኮ አሰፋ ካሳ፣ ሌ/ኮ ደምስ ሙሉጌታ፣ ሌ /ኮ ያሬድ ሽፈራሁ እና ክሳቸው የተቋረጠላቸው ኮ/ል አዜብ ታደሰን በተመለከተ በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል ቀርበው ከሐምሌ 25 ቀን እስከ ሀምሌ 29 ቀን 2014 መከላከያ ምስክርነታቸው ለመስማት ተቀጥሯል።

እንዲሁም ጡረተኛ ናቸው የተባሉ ቺፍ ኢንጂነር መላኩም አድራሻቸውን ፖሊስ አፈላልጎ ቀርበው መከላከያ ምስክርነታቸው እንዲሰማ መታዘዙን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply