የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን እድሳት በገንዘብ እጥረት ሳቢያ እየተጓተተ ሲሆን ለማጠናቀቅ 85 ሚልየን ብር ያስፈልጋል

በኢትዮጵያ የፓትሪያርክ ሹመት የሚፈጸምበቱ በቸኛ ስፍራ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የህንፃ እድሳት እንዲጠናቀቅ 85 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ሰበካ ጉባዔ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የህንፃ እድሳቱ እስካሁን 75 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን 90 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደፈጀ ተጠቁሟል።

የቤተ ክርስቲያኗ የእድሳት ሂደት ለ16 ወራት ያህል ጥናት ሲደረግበት ቆይቶ “በቅርስ እድሳት ልምድ ካለው” ቫርኔሮ ከተባለ ድርጅት ጋር በ172 ሚሊዮን ብር የሥራ ውል መጀመሩን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተረድታለች።

በዚህ የእድሳት ሂደት ከውጪ ለሚገቡ እቃዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች በሚል ግምት ህብረተሰቡ ለመርዳት ፍቃደኝነት አለማሳየታቸው እንደ ተግዳሮት ተጠቅሰዋል። ድጋፍ የሚሰበሰብባቸው መንገዶችም እንደቀጠሉ ነው።

እድሳቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ከግማሽ ገደማ ያስቆጠረ ሲሆን መጋቢት 30 ቀን 2016 እንደሚጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ለሦስት ወራት እንዲራዘም መደረጉን አዲስ ማለዳ ከታደመችበት መግለጫ ሰምታለች።

የቤተ ክስርስቲያኗ አስተዳዳሪ ሊቀ ስልጣን ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ እንደገለጹት እድሳቱ ከኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ የሚታደስ መሆኑን ጠቁመው በግንባታ ሂደት ያጋጠመ ችግር የለም ብለዋል።

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን በ1924 ከተመሰረተ ጀምሮ ከ90 ዓመታት በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል ፖትርያርኮች እና የሊቃነ ጳጳሳት በዓለ ሲመት የሚከናወንበትና በመካነ እረፍታቸው ጊዜም የማረፊያ ቦታ ሲሆን ለአገር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ግለሰቦችና የአገር መሪዎች መካነ መቃብር እንዲሁም ዘመናትን ያስቆጠሩ ቅርሶች ይገኙበታል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply