የቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ መተዳደሪያ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸደቀ፤ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የተሸኙት ደቀ መዛሙርቱ ከሰኞ ጀምሮ ይመለሳሉ

የቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ መተዳደሪያ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸደቀ፤ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የተሸኙት ደቀ መዛሙርቱ ከሰኞ ጀምሮ ይመለሳሉ

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬ ዓርብ፣ ጥቅምት 20 ቀን የቀትር በኋላ ውሎው፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያደገውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመተዳደሪያ ደንብ አጽድቋል፡፡

ምልአተ ጉባኤው አስቀድሞ የሠየመው የብፁዓን አባቶች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች እና ልዩ ልዩ ምሁራን ኮሚቴ፣ ከዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ጋራ በመኾን በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ያዘጋጁት የመተዳደሪያ ደንቡ፥ የመንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲውን ተጠሪነት፣ አደረጃጀት እና የዐዲስ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ በማስፋፋት እና በማጠናከር የሚመራበት መኾኑ ታውቋል፡፡

የመንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ለምልአተ ጉባኤው አቅርበውት በቅዱስ ሲኖዶሱ የጸደቀው የአንጋፋው ተቋም መተዳደሪያ ደንብ፣ በዐዲስ መልክ የተዘጋጀውን ሥርዐተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ በይዘቱም፣ የሚከተሉትን ዐበይት ለውጦች ማካተቱ ተጠቁሟል፤

ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የነበረው ተጠሪነቱ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ኾኗል፤

በዋና ፕሬዝዳንት እና በኹለት ማለትም በአካዳሚክ እና በአስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንቶች ይመራል፤ የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ፣ የዩኒቨርሲቲው ብፁዕ ፕሬዝዳንት ናቸው፤

የአገርን ታሪክ እና የውጭ የነገረ መለኰት ኮሌጆች ልምዶችን ያገናዘበ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ተደርጓል፤ ከቅድመ ምረቃ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ለሚጠናባቸው የትምህርት መርሐ ግብሮች፣ ሦስት ዋና ዋና የትምህርት ዘርፎች(Faculties) ተደራጅተዋል፤  

የመሠረተ እምነት(Faculty of Fundamental Theology – FFT)፣ የተግባረ እምነት(Faculty of Practical Theology – FPT) እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት(Faculty of Ethiopian Church Studies – FECS)ተደራጅተው፣ በየራሳቸው የዘርፍ ሓላፊዎች ይመራሉ፤

የትምህርት ዘርፎቹ በሥራቸው ልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነቶችን ያቀፉ 10 የትምህርት ክፍሎችን(Departments) እና በየትምህርት ክፍሎቹ የተካተቱ 311 የትምህርት ዓይነቶችን (ኮርሶችን) አካተዋል፤

በዐዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፣ ደቀ መዛሙርቱ በአራቱ ዓመት ቆይታቸው፣ የአብነት ትምህርቶችን በተጓዳኝ ቀስመው ለመውጣት እንዲችሉ፥ መጽሐፍ ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ዜማ ቤት እና አቋቋም ቤት ጊዜውን በዋጀ ዘመናዊ የማስተማሪያ ሥርዓት ተዘጋጅተዋል፤

በተጨማሪም፣ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት፣ ባሕላዊ የሕክምና ምርምር፣ የፍልስፍና እይታ፣ የቋንቋ ትምህርት፣ የሕግ ትምህርት እና የፍትሕ መርሕ፣ የመልካም አስተዳደር አመለካከት፣ የንግድ ሥራ አደረጃጀትና አስተዳደር ወዘተ አጉልቶ በማውጣት ያስታውቃል፤

በዩኒቨርሲቲው የሚሰጡ ትምህርቶችን በአገር ውስጥና በውጪ ኾነው በርቀት መማር ለሚፈልጉ ተማሪዎች በተደራጀ መንገድ ለማስተማር የE-Learning ማስተማሪያ ዘዴው ተሠርቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጎ አድማሱ ሰፍቷል፤

በሦስት ዓመት ለካህናት በአማርኛ እየተተረጎመ ሲሰጥ የቆየው፣ የልዩ ፕሮግራም ቴዎሎጂ ዲፕሎማ፣ ከተያዘው ዓመት ጀምሮ በአንድ ዓመት አጥሮ በሥልጠና ሰርቲፊኬት ይተካል፤

የአስተዳደር እና ልማት ዘርፎች በሰው ኃይል እና ቴክኖሎጂ ይጠናከራሉ፤ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማበልጸግ የሚያስችል ውል ተፈርሞ፣ ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፤

በሌላ በኩል፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሒደት ለማስጀመር፣ በጤና ጥበቃ እና በትምህርት ሚኒስቴር መመሪያዎች መሠረት፣ የቅድመ ጥንቃቄ ርምጃዎቹ እንደተጠናቀቁ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ተገልጿል፡፡ የመኝታ ክፍሎች፣ የመመገቢያ ካፊቴሪያዎች፣ የመማሪያ ክፍሎች እና ቢሮዎች፣ ለቅድመ ጥንቃቄው መራራቅ እና ምጣኔ ምቹ ተደርገዋል፤ በዛሬው ዕለትም የፀረ ተዋሕስያን ርጭት ሲካሔድ ውሏል፡፡ ከመጪው ሰኞ አንሥቶ፣ ነባር መደበኛ ደቀ መዛሙርቱ እንዲገቡ ጥሪ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡

መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲው፣ በቀኑ መርሐ ግብር በዐዲስ ገቢ ከሚቀበላቸው የመጀመሪያ ዓመት እና የድኅረ ምረቃ ተመዝጋቢዎች ጋራ እስከ 250 መደበኛ ደቀ መዛሙርት ይኖሩታል፡፡ ዛሬ በተጠናቀቀው የማታው መርሐ ግብር ምዝገባም፣ ከ1ሺሕ058 በላይ ተማሪዎች አሉት፡፡ የ2013 ዓ.ም. የትምህርትን ዘመን የሚጀምረው በታኅሣሥ ወር ሲኾን፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ፣ የዝጉን ወቅት የሚያካክስ ትምህርት በመስጠት፣ የመፈተንና የማጥራት ብሎም ደቀ መዛሙርቱን ለቀጣዩ ደረጃ የማመቻቸት ሥራ ይከናወናል፡፡

በቅድመ ጥንቃቄ መመሪያው መሠረት፣ ተማሪዎችን አራርቆ እና አመጣጥኖ የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስቀጠል፣ ዝግጅታቸው ከተጠናቀቁት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እና ዶርሚተሪዎች ባሻገር፣ የመምህራንንና የአስተዳደር ሠራተኞችን አበል መሸፈን ይጠበቅበታል፡፡ ይኸውም የመንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲውን ወጪ በማናሩ፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባቀረበው የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ዕቅድ፣ 30 ሚሊዮን ብር የወጪ በጀት መጠየቁ ተመልክቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እና ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት የመጠበቅ፣ የማስፋፋት እና የማጠናከር እንዲሁም ተጠሪነታቸውንና ደረጃቸውን የመወሰን ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአጠራር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እየተባለ ለቆየው የግማሽ ምእት ዓመት በላይ አንጋፋ የትምህርት ተቋም፣ የመተዳደሪያ ደንቡን በማጽድቅ በሕግ ወደ ዩኒቨርሲቲ አሳድጎታል፡፡ በተጨማሪም፣ ከዚሁ በማስከተል የቀረበውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፖሊሲ መርምሮ እንዲሠራት አጽድቋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ምልአተ ጉባኤው፣ የበጀት እና ሒሳብ መምሪያ አዘጋጅቶ ባቀረበው፣ የ2013 ዓ.ም. የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በጀት ረቂቅ ላይ በመወያየት፣ በሰጠው አስተያየት መሠረት ተስተካክሎ እንዲቀርብለት አዟል፤ በነገው ዕለት እንደሚያጸድቀው ይጠበቃል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply