“የበላይ የመንግስት አካል ከመለሳለስ ወጥቶ ዘላቂ ሕግ የማስከበር ሥራውን በመስራት ሕይወታችንን ሊታደግ ይገባል!” የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዎች አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 21 ቀን…

“የበላይ የመንግስት አካል ከመለሳለስ ወጥቶ ዘላቂ ሕግ የማስከበር ሥራውን በመስራት ሕይወታችንን ሊታደግ ይገባል!” የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዎች አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ/ም … አዲስ አበባ ሸዋ የበላይ የመንግስት አካል ከመለሳለስ ወጥቶ ዘላቂ ሕግ የማስከበር ሥራውን በመስራት ሕይወታችንን ሊታደግ ይገባል ሲሉ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡ ሰሞኑን በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር እና በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በተደረገ ጦርነት በርካታ የሰው ህይወት እና ንብረት መውደሙ ተገልጿል፡፡ የንብረት ውድመት ከደረሰባቸው የሸዋሮቢት ከተማ 05 ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደተናገሩት ፥ በመንግስት ቸልተኝነትና የላላ ሕግ የማስከበር ተግባሩ የተነሳ፤ በየአመቱ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ለኹሉም ማሕበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ወፍጮ ቤቶችና የንግድ ሱቆች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፤ መንግስት በዚህ ቀጠና ያለውን ጦርነትና የተደራጀ ቡድን ወይም ኃይል በማጥራት የመንግስትነት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰው ሕይወት ከመጥፋቱም ባሻገር የህዝብ መገልገያ ትምህርት ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የጤና ክሊኒኮች፣ ሱቆች፣ የቀበሌ አስተዳደር ቢሮዎች፣ የእስልምና ሀይማኖት መሪ መኖሪያ ቤት እንዲሁም የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች በታሰበና በታቀደ መልኩ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ እንዲጨምር በሚያደርግ መልኩ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውና መዘረፋቸውንም ጨምረው ገልጸዋል ስለዚህም የሚመለከተው የበላይ የመንግስት አካል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሕይወታችንን ሊታደግ ይገባል ሲሉ የቀበሌው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን የፌደራልና የክልል መንግስት የጸጥታ አካላት ጥቃቱን ለማስቆም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መስዋዕትነት እየከፈሉ ቢሆንም፤ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትና ንብረት ውድመት ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ሳይሆን አገርን የማጥፋት ተልዕኮ በማንገብና በተደራጀ አግባብ የሚፈጸም በመሆኑ ፈጣን የማጥራትና የሕግ የማስከበር እርምጃ ሥራዎችን መስራት አለበት ሲሉ ነዋሪዎቹ መግለጻቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡ አዲስ ማለዳ እንደዘገበው። አሸባሪ እና ወራሪ ኦነጋዊያን ከጥር 13/2015 ጀምሮ በሸዋ አጣዬ እና ሸዋሮቢት ዙሪያ በጸጥታ አካላት እና በማህበረሰቡ ላይ በፈጸሙት ጭፍጨፋ በርካታ አማራዎች መገደላቸው እና ሽህዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply