የበይነ መረብ ወይም ኦንላይን አገልግሎት እንሰጣለን በማለት የተለያዩ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ደላሎች ስላሉ ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡

የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የፓስፖርት አገልግሎትን ተገልጋዬች ባሉበት ቦታ ሆነው በኦንላየን ምዝገባ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ደሳለኝ ተሬሳ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ህገ-ወጥ ደላሎች ተገልጋዩን በማጭበርበር ሀሰተኛ ሰነዶችን በመስጠት እና በኦንላይን እንመዘግባለን በማለት የሚያጭበረብሩ አሉ ብለዋል፡፡በኤጀንሲው ዙሪያ ያሉና የክፍያ አገልግሎት ያለአግባብ የሚጨምሩ ፣ የተገልጋዩን መረጃ በጥራት የማይሞሉ፣ የተገልጋዩን ሳይሆን የራሳቸውን ስልክ ቁጥር በተገልጋዩ መረጃ ላይ በመፃፍ ለተገልጋዩ ተገቢው የፅሁፍ መልእክት እንዳይደርሰው የሚያደርጉ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

እንደ የልደት ምስክር ወረቀትና የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ያሉ አስፈላጊ መረጃዎችን በማጓደል ተጨማሪ ክፍያ የሚያስከፍሉ፣ የተጭበረበረ እና በሚመለከተው አካል ያልተረጋገጠ የልደት ሰርተፍኬት የሚያቀርቡ ህገ-ወጥ ደላሎች  መኖራቸዉን ደርሰንበታል ሲሉ አቶ ደሳለኝ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በማንኛውም አካባቢ ኢንተርኔት አገልግሎት ባለበት፤ የሞባይል ስልክ ወይም ኮምፒዩተር ላይ በመጠቀም ተገልጋዮች የኤጀንሲዉን ሊንክ ተከትለው በእራሳቸው ወይንም በሌላ ቅርብ የቤተሰብ አባል እንዲሞሉላቸው በማድረግ ቀጠሮ መያዝ እንደሚችሉም ኃላፊዉ ገልጸዋል፡፡

ቀን 06/08/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

The post የበይነ መረብ ወይም ኦንላይን አገልግሎት እንሰጣለን በማለት የተለያዩ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ደላሎች ስላሉ ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡ appeared first on አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን.

Source: Link to the Post

Leave a Reply