የባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ሽኝት ተደረገለት፡፡ አሻራ ሚዲያ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ. ም ባህርዳር – ኢትዮጵያ…

የባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ሽኝት ተደረገለት፡፡ አሻራ ሚዲያ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ. ም ባህርዳር – ኢትዮጵያ የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ጥሪውን የተቀበሉ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ዛሬ ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡ አሸባሪው ትህነግ ለአማራ ሕዝብም ኾነ ለመላው ኢትዮጵያውያን ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ለማጥፋት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የክተት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ለቀረበው ጥሪ ከኹሉም የክልሉ አካባቢዎች ተግባራዊ ምላሽ እየተሰጠ ነው፡፡ በባሕር ዳር ከተማ መሠረታዊ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱና የክተት ጥሪውን የተቀበሉ የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝባዊ ሠራዊቱ የሚሰጠውን የግዳጅ ቀጣና በብቃት እንደሚሸፍኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ተጨማሪ ኃይል አሰልጥኖ የማሰማራት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ሌሎች ወጣቶችም የከተማቸውን ሰላም እየጠበቁ ለቀጣይ የቤት ሥራ እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ ዘማች የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በቂ ወታደራዊ ስልጠና ማግኘታቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ ንጹሐን እየተገደሉ፣ ሴቶች እየተደፈሩ፣ አርሶ አደር የዘራው ሰብል በወራሪ እየታጨደ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም ብለዋል የሕዝባዊ ሠራዊት አባላቱ፡፡ አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፈል ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ቆርጠው መነሳታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ ካልባሌ ቦታ እና ከሱስ ተጋላጭነት ራሱን ነጻ በማውጣት መደራጀት፣ መታጠቅና መዝመት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ መሪዎች ወጣቶችን በማስተባበር ወደ ግንባር እንዲዘምቱ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች ድህረ ገፃችንን ይጎብኙ! Facebook:-https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን!

Source: Link to the Post

Leave a Reply