የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ በግብር አሰባሰብ አርአያ ለሆኑ ነጋዴዎችና ተቋማት ዕውቅና ሰጠ፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ በግብር አሰባሰብ አርአያ ለሆኑ ነጋዴዎችና ተቋማት ዕውቅና ሰጠ፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ “ግልፅ አሠራር እዘረጋለሁ፣ ተጠያቂነትን አሰፍናለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ በ2012 በጀት ዓመት በነበረው የገቢ አሰባሰብ ሂደት ጉልሕ ድርሻ ላበረከቱ ግብር ከፋዮች፣ ባለሙያዎችና ተቋማት ዛሬ በባሕር ዳር ዕውቅና ሰጥቷል።

ዕውቅናና የምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ዐሊ ዑመር ኤሌክትሮኒክስ አንዱ ነው። ድርጅቱን ወክለው የዕውቅና የምስክር ወረቀቱን የተቀበሉት ወይዘሪት ነስራ የሱፍ ግብርን መክፈል ግዴታና የሞራል ልዕልና በመሆኑ ድርጅቱ በታማኝነትና በወቅቱ ግብሩን ከፍሏል ብላለች።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለኢየሱስ ፀጋዬ የገቢ ተቋማትና የገቢ አሰባሰብ ሥራው እንዲነቃቃ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የገቢ ተቋሙ እና የከተማ አስተዳደሩ ባደረጉት ርብርብ በ2013 ዓ.ም የኮሮናቫይረስና የጸጥታ ችግሮችን በመቋቋም ከታቀደው 2 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ውስጥ በግማሽ ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል። ይህ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ላደረጉ ምሥጉን ግብር ከፋዮችና ለገቢ ባለሙያዎች እውቅና መስጠትም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ በአጠቃላይ መሰብሰብ ከነበረበት 50 በመቶ እደኾነም ጠቁመዋል። የተሰበሰበው ገቢ በከተማ አስተዳደሩና በክልሉ የሚነሱትን የልማት ጥያቄዎች የሚመልስ ስላልኾነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ገቢ መሰብሰብ እንደሚጠበቅባቸው ኃላፊው አስገንዝበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሣኅሉ (ዶክተር) በየዓመቱ ለተመዘገበው የገቢ ዕድገት የንግዱ ማኅበረተሰብ፣ የልማት ድርጅቶች፣ የመንግሥት ተቋማትና የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ እስከ ታችኛው መዋቅር ገቢ መሰብሰብ ሀገር እንደሀገር የማስቀጠልና ሥርዓት የመገንባት አጀንዳ እንደሆነ በመገንዘብ ያስመዘገቡት ውጤት ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባው። ከተማ አስተዳደሩ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ሲገባው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብቻ መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የገቢ ተቋሙ መሪዎችና የባለሙያው ቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም የግብር ከፋዮች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው በበጀት ዓመቱ የታቀደዉን ያክል ለመፈጸም እንዳልተቻለ ዶክተር ድረስ ጠቁመዋል። የገቢ ተቋማትም ቢኾኑ ያለባቸውን ክፍተቶች በማስተካከል፣ የንግድ ማኅበረሰቡ በታማኝነት ገቢዉን በመክፈል በቀሪ ወራት ውጤታማ የግብር አሰባሰብ ሥራ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

“በባሕር ዳር ያለው ግብር ከፋይ ግብርን ማጭበርበር የሕዝብን አደራ መብላት እንደሆነ ተረድቶ ለሕግ ተገዢ በመሆን የሚጠበቅበትን ግብርና ታክስ በወቅቱ በመክፈል የሀገር ኩራትና አለኝታ መሆኑን እንዲያረጋግጥና የተጀመረው ልማትም ዳር እንዲደርስ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባዋል” ብለዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ብዙዓየሁ ቢያዝን የሚከበር ባለሙያ፣ መሪና ነጋዴ ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል። የታክስ ሥርዓት መገንባት ሀገር መገንባት ነው ያሉት ኃላፊዋ ሁሉም ዜጋ ለወገኑና ለሀገሩ በታማኝነት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል። 30 ታማኝ ግብር ከፋዮች፣ 2 የገቢ ተቋሙ ሠራተኞች፣ 3 ክፍለ ከተማ በ2012 ዓ.ም በገቢ አሰባሰብ አርአያ በመሆናቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ተማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ በግብር አሰባሰብ አርአያ ለሆኑ ነጋዴዎችና ተቋማት ዕውቅና ሰጠ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.

Source: Link to the Post

Leave a Reply