የባንኮች ተቀማጭ ሂሳብ 2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር መድረሱን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ 

ግንቦት 13 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ባንኮች ተቀማጭ ሂሳብ 2.4 ትሪሊየን ብር መድረሱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስቴሩ በተመረጡ አገራዊ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ከፍተኛ ዕድገት ታይቷል ተብሏል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚችል ትንበያ ተቀምጦ እንደነበር አስታውሰው ይህ የሚሳካበት ሁኔታን የሚያመላክት አፈጻጸም አለ ብለዋል።

ግብርና ለጥቅል አገራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፆ እያበረከተ የቀጠለ ሲሆን “ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዋና ዋና ሰብሎች ልማት ከአምና ተመሳሳይ ጊዜ ተጨማሪ ከ100 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት” ተገኝቷል ተብሏል።

በቡና፣ በእንሰሳት ሀብት ልማትና በሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቶች ውስጥ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ስጋ፣ ወተት፣ ዓሳ እና ማር በማካተት የተያዩ ድጋፎችን በማድረግ የተገኙ ውጤቶች እንዳሉ ማወቅ ተችሏል።

በግብርናው ዘርፍ ለጥቅል አገራዊ ምርት (GDP) የሚኖረው አስተዋፆ አምና ከነበረው ተጨማሪ በመኖሩ የተቀመጠውን የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ የሚሳካ እንደሆነ አዝማሚያዎቹ ያሳያሉ ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በኢንደስትሪ እና የአምራች ዘርፍ ከአምናው የተሻለ አፈፃፀም እንደታየም ገልጸዋል።

2.5 ቢሊየን ዶላር በሸቀጦች የውጭ ንግድ ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ በትራንስፖርት ዘርፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምና በዘጠኝ ወር ከነበረው አፈጻጸም በ25 በመቶ የበለጠ ማደጉን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply