You are currently viewing የቤተልሔም ታፈሰ ሁለተኛ መጽሐፍ ለገበያ ሊውል ነው

የቤተልሔም ታፈሰ ሁለተኛ መጽሐፍ ለገበያ ሊውል ነው

በአሁኑ ወቅት በስርጭት ላይ በሌለው “ኤል ቲቪ” ቴሌቪዥን ጣቢያ ታቀርባቸው በነበሩ አነጋጋሪ ቃለ መጠየቆቿ የምትታወቀው ቤተልሔም ታፈሰ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ታሪኮች የያዘ ሁለተኛ መጽሐፏን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለንባብ ልታበቃ ነው። “አምስት ጉዳይ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ መጽሐፍ፤ በኦሮሞ ትግል ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ ሰዎች አንዱ የሆነውን የባሮ ቱምሳ “ትክክለኛ ገዳይ” ማንነት እና አማሟቱን በዝርዝር የያዘ ነው። 

“አምስት ጉዳይ” ቤተልሔም “ራሳቸውን እንደ ኮከብ የሚያዩ” ስትል የምትገልጻቸውን “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋንያን” ማንነት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል። በአምስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ220 ገጾች በተዘጋጀው በዚህ መጽሐፍ፤ እንደ ደራሲያዋ የመጀመሪያ ስራ ሁሉ የጃዋር መሐመድ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ሌንጮ ለታ ታሪኮች ተካትተውበታል። 

“እኔ እና የኤልቲቪ ምስጢሮቼ” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ያልነበሩት፤ ልደቱ አያሌው እና ነአምን ዘለቀ በአዲሱ መጽሐፍ ቦታ አግኝተዋል። ስማቸው በይፋ ያልተገለጸ ባለሀብቶች እና ባለስልጣናት አጫጭር ገጠመኞችም፤ እንደ ማዋዣ ከቀረቡት የደራሲዋ የጉዞ ታሪኮች ጋር ተዳምረው የመጽሐፉ አካል ሆነዋል። የጉዞ ታሪኮች የተካተቱት “ደረቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ ከማቅረብ ይልቅ አንባቢን እያንሸራሸሩ መረጃ ለመስጠት” በማሰብ መሆኑ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል።

“ወደ ስምንት ዓመታት በሚጠጋው የሚዲያ ስራዬ፤ በሃገራችን ውስጥ የሚከወኑ ጉዳዮችን አይቻለሁ። በኢትዮጵያ ባሉ፤ በገዘፉ፣ በሁሉም የእምነት ቦታዎች ምን ምን እንደሚከወን ተገንዝቤአለሁ። ወደፊትም እመረምራለሁ” ስትል በመጽሐፉ መንደርደሪያ ላይ ያሰፈረችው ቤተልሔም፤ “አምስት ጉዳይን” የጻፈችው “ችግሮቻችንን ካወቅን፣ ሰላማዊ ዛሬን እንፈጥራለን በሚል ተስፋ ብቻ” መሆኑን ገልጻለች። 

የመጽሐፉ መጠሪያም “ከተስፋ ጋር” የተያያዘ መሆኑንም ደራሲዋ አስረድታለች። “ልጅነቴ ወቅት በቤታችን የነበረው የግድግዳ ሰዓት ላይ አንጋጥጬ፤ አምስት ጉዳይ መሆኑን ለሰዓት ጠያቂዎቼ አበስር የነበረበትን ሁኔታ በማስታወስ፤ ጊዜ ለሰዎች የሚሰጠውን ተስፋ ለማንጸባረቅ ነው” ስትልም ቤተልሔም የመጽሐፉን ስያሜ አመጣጥ  አብራርታለች።

“ኤል ቲቪ” በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰራችበት ወቅት ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሳምንታዊ የቃለ መጠየቅ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ የነበረችው ቤተልሔም፤ ጣቢያውን ከለቀቀች በኋላ በከፈተችው የዩቲዩብ ቻናልም የተለያዩ እንግዶችን በመጋበዝ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ ስታነጋግር  ቆይታለች። በዚህ የሙሉ ጊዜዋ ስራ ምክንያት “ከኦሮሞ ፓለቲካ ጋር ግንኙነት ያላቸው” እንግዶችን እንደምታገኝ የጠቆመችው ደራሲዋ፤ ይህም “የኦሮሞን ህዝብ የፓለቲካ ትግል ታሪክ ለማወቅ” ታደርግ ለነበረው ጥረት ዕድሎችን እንዳመቻቸላት ጽፋለች። 

“ከትላንት ታሪክ መማር የብልህ ህዝቦች መለያ ነው። ትላንት ምን ላይ ነበርን? ዛሬ እዚህ እንዴት ተገኘን? ነገ የት እንደርሳለን? ብሎ ለመተለም፤ ትላንትን የመሰለ አስተማሪ የለም” የምትለው ቤተልሔም፤ በዚህ እሳቤ መነሻነት የባሮ ቱምሳን አሟሟት ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ትገልጻለች። “ ‘ባሮን ማን ገደለው?’ የሚለው ጥያቄ “ጥርት ያለ ምላሽ ሳይሰጠው” እና “አንዱ በሌላው ላይ ጣት እየተቀሳሰረ” መቆየቱንም ታስረዳለች። 

“አንዳንድ ታሪኮች ርእስ የላቸውም፤ ተነግረው እንዳልተነገሩ ይረሳሉ። አንዳንድ ሰዎች አስታዋሽ የላቸውም፤ ኖረው እንዳልኖሩ ይቆጠራሉ። አንዳንድ ገድሎች አልተዘከሩም፤ የባከኑ መስዋዕትነቶች ይባላሉ። አንዳንድ ቅሌቶች ሰው ፊት አልታዩም፤ እንዳልተፈጸሙ ሁሉ በጨለማ ውስጥ ይቀራሉ። አንዳንድ አወዳደቆች ከትዝብት ውጭ ከሆኑ፤ ልብሳችንን አራግፈን እንቀጥላለን። አንዳንድ እውነቶችም፥ ተረስተዋል፤ ተጋርደዋል። ዙሪያውን ለመታሰቢያነት የቀረላቸው ምንም የለም። አንዳንድ ኮቴዎች በመረሳት ተጠቅተዋል። አንዳንድ ወኔዎች ለሞት ዳርገዋል” ትላለች ቤተልሔም ስለዚህ ጉዳይ በምታወሳበት የመጽሐፏ ክፍል።

ባሮ በኦሮሞ ህዝብ የፓለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ “በአጭር ከተቀጩ ታጋዮች አንዱ ነው” የምትለው ቤተልሔም፤ በእርሱ ላይ የተፈጸመው ግድያ “የኦሮሞን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ ድርጀቶች አንድነታቸው እንዲናጋና ትግላቸው እንዲጓተት ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ ነው” ስትልም አጽንኦት ትሰጣለች። “ ‘ባሮ ቱምሳን ማን ገደለው?’ የሚለው ጥያቄ፤ ከብዙ ድካም በኋላ ምላሽ ያገኘሁለት ጥያቄ ሆኗል” የምትለው ቤተልሔም፤ የግድያው ቀን ውሎ እና የአገዳደሉ ሁኔታ በመጽሐፏ በዝርዝር ከትባለች። 

ደራሲዋ የባሮን ገዳይ ለማወቅ፤ ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁት ሌንጮ ለታ እና ጄይሉ የተባሉ የቀድሞ የኦነግ ከፍተኛ አመራር ጋር ያደረገችውን የመጀመሪያ ቀን ቆይታ፤ በመጽሐፏ የጀርባ ሽፋን ላይ ቀንጭባ አቅርባለች። ሌላው በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ቦታ የተሰጠው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ነው። ደራሲዋ ጃዋር በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስሮ በነበረበት ወቅት ለመጠየቅ ሄዳ ያጋጠማትን እና የተነጋገሩትን፤ ለመጽሐፏ የጀርባ ሽፋን ማስተዋወቂያነት መርጣዋለች።

የጃዋር ጉዳይ ከልደቱ አያሌው፣ ከቄሮ ትግል እና ከእስር ጋር ተጣምሮ በመጽሐፉ ከተሰጠው አንድ ሙሉ ምዕራፍ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይነሳል። ደራሲዋ በአንደኛው የመጽሐፏ ክፍል ላይ “ጃዋር መሐመድ በፖለቲካው የከሰረ ይመስላል። ምናልባት ሁለተኛ ዕድል አግኝቶ እንደ ገና ማንሰራራት ከቻለ እናያለን። እንደ እኔ ግን፥ ከማያቸው ሁኔታዎች፥ ጃዋር መሐመድን እንደ ገና በዚያ ፖለቲካ ውስጥ ለማየት ተአምር መምጣት አለበት” ስትል በፖለቲከኛው ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም አንጸባርቃለች። 

ቤተልሔም ይህን መሰል አቋሟን በሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ላይም ታራምዳለች። “ኦሮሞ ግን ምንድነው የሚፈልገው?” የሚለው ጥያቄዋ በመጽሐፏ ደጋግሞ ይነሳል። “እጅግ የከፋ ስርዓታዊ በደል የደረሰበት የኦሮሞ ህዝብ ፍትህ እንዲያገኝ፤ የፖለቲካ ልሂቃን ከ50 ዓመታት በላይ በብሔሩ ስም ታግለዋል። እነዚህ ሰዎች፤ ከውስጥም ከውጭም በነበሩባቸው ጫናዎች እና የእርስ በእርስ ፍትጊያዎች ምክንያት፤ የህዝቡ የነጻነት፣ የእኩልነት እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ቀናት እንዲዘገዩ ሆነዋል” ትላለች ቤተልሔም በመጽሐፏ።  

“ [የኦሮሞ ህዝብ ትግል] መጠራጠር፣ ፍረጃና ፉክክርን ትቶ ሰብሰብ በማለት፥ ለአንድ ህዝብ አንድ ጠንካራ ድርጅት ከመመስረት ይልቅ፤ በሰፈር እና በመንደር እየተሰባሰቡ መከፋፈል መለያው ሆኖ ዘልቋል”

ቤተልሔም ታፈሰ – “አምስት ጉዳይ” መጽሐፍ

“አንዳንድ የፓለቲካ ተንታኞች፦ ለትግሉ መዘግየት የውጫዊ ጫናዎች መሰናክልነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ውስጣዊ ሽኩቻው ግን ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ይናገራሉ። መጠራጠር፣ ፍረጃና ፉክክርን ትቶ ሰብሰብ በማለት፥ ለአንድ ህዝብ አንድ ጠንካራ ድርጅት ከመመስረት ይልቅ፤ በሰፈር እና በመንደር እየተሰባሰቡ መከፋፈል መለያው ሆኖ ዘልቋል” ስትልም ትችቷን በመጽሐፏ ላይ አስፍራለች። 

እነዚህን እና ሌሎች ጉዳዮች የተካተቱበት “አምስት ጉዳይ” መጽሐፍ ህትመቱ መጠናቀቁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገረችው ቤተልሔም፤ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ባሉት ቀናት ገበያ ላይ እንደሚውል ገልጻለች። በ400 ብር ዋጋ ለገበያ የሚቀርበውን ይህን መጽሐፍ፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የተለያዩ የክልል ከተሞች ከሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ እንደሚሰራጭ ደራሲዋ አስታውቃለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply