የቤተክርስቲያኒቱ የይቅርታ ጥያቄ ከልብ እና የትግራይን ሕዝብ የሞራል ስብራት የሚጠግን ሊሆን ይገባል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የይቅርታ ጥያቄ ከልብ እንዲሁም የትግራይን ሕዝብ የሞራል ስብራት የሚጠግን ሊሆን ይገባል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሚመራ የልዑካን ቡድን ጋር በትናንትናው ዕለት በመቀለ በተገናኙበት ወቅት ነው፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከኹለት ዓመታት በላይ ሲደረግ በነበረው አስከፊ ጦርነት ከፍተኛ የሆነ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ስብራት ደርሶበታል ያሉት ፕሬዘዳንቱ የይቅርታ ጥያቄው ከልብ እንዲሁም ይህን የሚክስ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሲባል እንደዚህ አይነት ሕዝብን የሚያራርቁ ክስተቶች ሲፈጠሩ አይመለከተውም ማለት ባለመሆኑ፣ በትግራይ ያሉ ብፁዓን አባቶችን በተደጋጋሚ እንዳናገሯቸው ጠቅሰዋል።

ባናገርኳቸው ወቅትም የትግራይ ሕዝብን እንደ ጭራቅ ሲስሉ በነበሩ እንዲሁም <<ከትግራይ ሕዝብ ይልቅ ከሰይጣን ጋር ብናመልክ ይሻለናል>> እና የመሳሰሉ ከቤተክርስትያን አባቶች የማይጠበቁ የጥላቻ ንግግሮች ሲናገሩ በነበሩ አንዳንድ የእምነት አባቶች እጅግ ማዘናቸውን እና ስሜታቸው እንደተጎዳ ተናግረዋል ብለዋል፡፡

እነዚሁ አባቶች በተደጋጋሚ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደዚህ ዓይነት ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግር ሲያደረጉ በግልም ሆነ ቤተክርስቲያኒቱ እንደ መዋቅር ለማስቆም አለመሞከሯ በትግራይ የሚገኙ ብፁዓን አባቶችን እና የዕምነቱን ተከታይ ማሳዘኑን ፕሬዘዳንቱ አውስተዋል።

ልዑኩ በመቐለ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፍያ ሲደርስ በትግራይ ጊዚያዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ በተለያዩ ማህበራት የማህበረሰብ ወኪሎች እና ወጣት ዘማርያን ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል ተብሎ አስቀድሞ ቢገለጽም በሥፍራው የትግራይ ክልል የኃይማኖት አባቶችና፣ ዘማርያን አለመገኘታቸው ታውቋል።

ለዑኩን የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለብፁዓን አባቶች ጥሪ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በምን ምክንያት እንደቀሩ አናውቅም ያሉ ሲሆን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዘዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው “እኔም የትግራይን ብፁዓን አባቶች በዚህ መድረክ ካልተገኛችሁ ከእከሌ ጋር ካላወራችሁ ብዬ ጫና የመፍጠር እና የማስገደድ ሞራል የለኝም” ብለዋል።

ፓትርያርኩ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በፌዴራል ምንግሥት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት በዚሁ እንዲቀጥል ሕዝቡም እረፍት እና ሰላም እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡ 

በትግራይ ክልል ከኹለት ዓመታት በላይ የዘለቀው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ቤተክርስቲያን ማድረግ ያለባት በወቅቱ ባለማድረጓ ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ቤተክርስቲያኒቱ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ እንዱሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጋለች፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply