የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የማስጠበቅ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ በሰንበት ት/ቤቶች ይመራል

የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የማስጠበቅ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ በሰንበት ት/ቤቶች ይመራል

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G
  • 13 ብፁዓን አባቶች ያሉበት በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ኮሚቴ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ጥቃት ጉዳይ መንግሥትን ያነጋግራል
  • 5 ብፁዓን አባቶች ያሉበት በቅዱስነታቸው የሚመራ ሌላ ኮሚቴ ደግሞ፣ በቅራኔ ያሉ የፖሊቲካ ኃይሎችን  በግንባር ያነጋግራል
  • ዛሬን ዕረፍት ያደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ መደበኛ ስብሰባውን በመጪው ሰኞ ይቀጥላል፤

***

ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በተዘረጋው መዋቅር ተደራጅተው ለቤተ ክርስቲያን ዘብ እንዲቆሙ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አዟል፤ ኦርቶዶክሳውያን የሕግ ባለሞያዎችም፣ በየአህጉረ ስብከቱ እየተደራጁ እና ከቤተ ክርስቲያን ውክልና እየተሰጣቸው ግፈኞችን እንዲፋረዱ ወስኗል፡፡

ጉባኤው፣ በትላንት ዓርብ ከቀትር በኋላ ውሎው፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተባባሱ የመጡ በደሎችንና ጥቃቶችን ለማስቆም በሚያስችሉ አማራጮች ተወያይቷል፡፡ በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ ለተደጋጋሚ ጥቃት እየተዳረጉ፣ የግፍ ግፍ እየተፈጸመባቸው ለሚገኙ ምእመናን የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ እና ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠል፣ ወጣቶችንና ምእመናንን በአንድነት አስተባብሮ እና አደራጅቶ ራስን በራስ ለመጠበቅ መትጋት፣ አማራጭ እንደሌለው መተማመን ላይ ደርሷል፡፡

በመኾኑም፣ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ወጣቱን ትውልድ አቅፈው ከአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ጀምሮ ሱታፌ በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ በሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች ግንባር ቀደም አመራር፣ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ከላይ እስከ ታች ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን ከጥቃት እንዲከላከሉ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም፣ በሞያቸው እና በገንዘባቸው ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱት አገልግሎትና ድጋፍ በጥናት እየተለየ፣ ኾነ ተብሎ የሐሰት ክሥ እየተፈረከባቸው እና የሐሰት ምስክር እየተዘጋጀባቸው በእስር እየተንገላቱ ላሉት ምእመናን፣ የሕግ ባለሞያዎች በየአህጉረ ስብከቱ እየተደራጁ እና ውክልና እየተሰጣቸው ጥብቅና እንዲቆሙላቸው እንዲደረግ፣ ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ ዞኖች፣ ምእመናን በሕይወታቸው እና በንብረታቸው የሚደርስባቸው ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ውድመት እና መፈናቀል ሳይበቃ፣ አላግባብ ታስረው የሚንገላቱ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት እና አባላት፣ በመንግሥት የተወሰደውን የመስቀል ደመራ እና የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ዐደባባዮችን ለማስመለስ ክትትል የሚያደርጉ የቤተ ክርስቲያን ወኪሎች(ሠራተኞች፣ ካህናት እና ምእመናን) መኖራቸውን የጠቀሰው ምልአተ ጉባኤው፣ በትሩፋት የሚያገለግሉ የሕግ ባለሞያዎች በየአህጉረ ስብከቱ ውክልና እየተሰጣቸው ግፈኞቹንና አጥቂዎቹን እንዲፋረዱላቸው ወስኗል፡፡

በውጪ አህጉረ ስብከት ያሉ የሕግ ባለሞያ ምእመናንም፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘንበውን ጥቃት እና ሥቅየት እየተከታተሉ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ተቋማት በልዩ ልዩ መንገዶች በማሳወቅ፣ የጥፋት ድርጊቱን ለማስቆም የተደራጀ ግፊት እንዲያደርጉ ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ አያይዞም፣ በስሑት ርእዮተ ዓለም እና በሐሰተኛ ትርክት እየተመሩ፣ ቤተ ክርስቲያን ባልዋለችበት ያለስሟ እና ያለግብሯ ታሪኳንና ገጽታዋን ለማጠልሸት ያለማሳለስ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እና ግለሰቦች፣ በውጪው ክፍላተ ዓለም በብዛት እንዳሉ ጉባኤው አውስቷል፡፡

እነኚህም፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም እና ለማፈራረስ በቀጥታ እና በእጅ አዙር የሚሹ ኃይሎች እና ቅጥረኞቻቸው በመኾናቸው፣ በተለይ በአውስትራልያ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በካናዳ ያሉ የሕግ እና ተጓዳኝ መስኮች ባለሞያዎች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ወዳጆች፣ እንቅስቃሴያቸውን እየተከታተሉ እንዲያጋልጧቸው በሕግም እንዲፋረዷቸው ምልአተ ጉባኤው አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው፣ በየጊዜው ቅርፃቸውን እየለዋወጡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት፣ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ለመግታት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በማእከል እና በየደረጃው ኹለት አካላትን እንዲያቋቁም ቀደም ሲል ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው፥ የቅድመ አደጋ ስጋት ክትትል እና የማስጠንቀቂያ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 39ኛ ዓመታዊ ስብሰባ በጋራ መግለጫው እንዳሳሰበው፣ ይህ የማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ ቅምጥ አደጋ እና ስጋት ያለባቸውን የአገራችንን ክፍሎች አስቀድሞ እየለየ፣ በመረጃ፣ ጥናትና ትንተና ይከታተላል፤ ጉዳት እንዳይደርስ ያነቃል፤ ያስጠንቅቃል፤ ከደረሰም ስለ ጉዳቱ መረጃ አሰባስቦና ተንትኖ የመቋቋሚያ ስልት ይቀይሳል፡፡ በዚኹ ተግባር ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሠራውን አካል፣ በማእከል እና በአህጉረ ስብከት በየደረጃው የማቋቋሙ ሒደት በአስቸኳይ እንዲጀመር ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አስፈጻሚውን ጠቅላይ ጽ/ቤቱን በጥብቅ አሳስቦታል፡፡

ከዚኹ ጋራ በትይዩ፣ ለድንገተኛ አደጋ እና ችግሮች ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥ አካል በማእከል እንዲቋቋም ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘንበው መከራ በአጭር ጊዜ ይቆማል ተብሎ ስለማይገመት፣ ለአስቸኳይ ርዳታ እና መልሶ ማቋቋሚያ የሚኾን ልዩ ልዩ ግብአት እና ገንዘብ፣ በዚኹ አካል አስተባባሪነት በአንድ ቋት እንዲሰበሰብ ነው ምልአተ ጉባኤው የወሰነው፡፡ አደጋ ባጋጠመ ጊዜ፣ ዝግጅት አድርጎ ፈጥኖ እየደረሰ ርዳታ እና ድጋፍ ለሚያደርገው ለዚኽ አካል፣ በተለይ የውጪ አህጉረ ስብከት፣ ምእመናንንና ገባሬ ሠናያትን ከወዲሁ እያስተባበሩ የቁሳቁስ፣ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ እና የሞያ ኹለገብ እገዛ በማድረግ እንዲያጠናክሩት ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

በተያያዘ ዜና ምልአተ ጉባኤው፣ የቤተ ክርስቲያን ጥቃት እንዲቆም እንዲሁም፣ “የአገር ሰላም ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተናል፤” በሚል የዕርቅንና የአንድነትን ጉዳይ፣ ከመንግሥት እና ከፖሊቲካ ኃይሎች ጋራ የሚነጋገሩ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመሩ ኹለት ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን በትላንቱ የቀትር በኋላ ውሎው አቋቁሟል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ጥቃት አስመልክቶ መንግሥታዊ አካላትን የሚያነጋግረው ኮሚቴ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ 13 ብፁዓን አባቶችን የያዘ ነው፡፡ በኦርቶዶካሳዊነታችን ብቻ የሚደርስብን ጥቃት፣ እንግልት፣ ሥቅየት፣ መገፋት በአስቸኳይ እንዲቆም ከማሳሰብ ባሻገር፤ ለተገደሉት እና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ካሳን፣ ለተፈናቀሉት መመለስን፣ በግፍ ለታሰሩት መፈታትን፣ በኃይል ለተወሰዱት የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎቻችን መመለስን፣ ከአስቸኳይ ዐዋጅ ማብቃት በኋላ በኮሮና ቫይረስ ሰበብ በአድልዎ ለተከለከሉት የዐደባባይ በዓሎቻችን በእኩልነት የመስተናገድ ፍትሐዊነትን ይጠይቃሉ፡፡

በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የአገር ሰላምን ጉዳይ አስመልክቶ በተቃርኖ ያሉ ኃይሎችን በግንባር አግኝተው የሚያነጋግሩ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመሩ አምስት ብፁዓን አባቶችን በአባልነት የያዘ ሌላ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ በየትኛውም የአገራችን አካባቢዎች በሚደርሱ ጥቃቶች፣ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ዋጋ እየከፈሉ ያሉት፣ በአገር ሰላም ስለሌለ እንደኾነ ምልአተ ጉባኤው ጠቅሶ፣ ይህም፣ የፖለቲካ ትርምሱ እና መሳሳቡ ቀጥተኛ ውጤት እንደኾነ ገልጿል፡፡

በአገር የሰላም ዕጦት ምእመናን ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ሲያጡ ከማየት የበለጠ የቤተ ክርስቲያን ጥቃት ባለመኖሩ፣ “የአገር ሰላም ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተናል፤” በሚል በቅራኔና ፍጥጫ ውስጥ ያሉትን የፖሊቲካ ኃይሎች፣ በግንባር በማግኘት እና በማነጋገር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠንክሮ ለመማፀን ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ “አገር እየተበደለ እና እየጠፋ፣ ሕዝብም እያለቀ ያለው በፖሊቲካው ትርምስ ምክንያት ነው፤” ያለው ምልአተ ጉባኤው፣ ቤተ ክርስቲያን ተጎጂ ብትኾንም የማስታረቅ ሚናዋን እንድትወጣ፣ ለዚህም ኮሚቴው በአስቸኳይ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

ቅዱስነታቸውን ጨምሮ በኮሚቴው አባልነት የተመረጡት አምስቱ ብፁዓን አባቶች፥ የስዊድንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ጎርጎሬዎስ፣ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የሰሜን ወሎ እና ከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የውጭ ጉዳይ መምሪያ እና የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ናቸው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከትላንት በስቲያ የጀመረውን የዓመቱን የመጀመሪያ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ፣ በመጪው ሰኞ ይቀጥላል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply