የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጅግጅጋ ከተማ ተከበረ

የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጅግጅጋ ከተማ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 15ኛው የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የተለያዩ ክልል ተወካዮች በተገኙበት በጅግጅጋ ከተማ ተከበረ፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፣ የሃረሪ ክልል አፈጉባኤ አድሰአለም በዛብህ ፣በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን፣ የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ሻሌን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት እና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ብሄር ብሄረሰቦች ተገኝተዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን “እኛ ኢትዮጵያውያን ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን፣ ከሚያራርቁን ይልቅ የሚያስተሳስሩን ለዘመናት አብሮ በመኖር ያዳበርናቸው በርካታ የጋራ እሴቶች አሉን” ብለዋል፡፡

እነዚህን የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ በማጠናከር በሕዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት የበለጠ ስር እንዲሰድ መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ በሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ቃል የፈፀመው የህወሓት ቡድን ላይ እየተወሰደ ባለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ሁሉም ብሄርና ብሄረሰቦች ከመከላከያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ “እኩልነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ለብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው ፡፡

በተያያዘም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከህዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቆይታ የነበረውን እና የ15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቀን በዓል አካል የሆነውን ችቦ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ተረክቧል፡፡

ችቦውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፋጡማ ሙስጠፋ በአሶሳ ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስረክበዋል፡፡

 

The post የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጅግጅጋ ከተማ ተከበረ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply