የተመድ ስደተኞች ኮሚሽነር በትግራይ የኤርትራ ስደተኞች በአየር ጥቃት ደረሰባቸው አሉ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በትግራይ ውስጥ በማይ አይኒ ስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ በተካሄደ የአየር ጥቃት ሁለት ህጻናትን ጨምሮ ሦስት የኤርትራ ስደተኞች መገደላቸው መስማታችን በጣም አሳዝኖኛል ሲሉ ተናገሩ፡፡

ከስፍራው በደረሰን መረጃ መሠረት ሌሎች አራት ስደተኞችም ቆስለዋል ሲሉ የተናገሩት ኮሚሽነሩ ዩኤንኤችሲአር የህክምና እርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ስደተኞች ጨርሶ የጥቃት ኢላማ መደረግ የለባቸው ያሉት ኮሚሽነር ግራንዲ ዩኤንኤችሲአር በቦታው የተፈጸመውን በዝርዝር ማጥናቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ድርጅታቸው ሁሉም ወገኖች ስደተኞችን ጨምሮ የሰለማዊ ሰዎችን መብቶች እንዲያከብሩ ጠይቀዋል፡፡  

በሌላም በኩል የህወሓት አመራር አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድሮኖች በዶሮ ሀፋሽ አክሱም እንዳባጉናና ሽሬ ላይ ባደረሱት ብዙ ሰለማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሲሉ ትናንት ባወጡት የትዊት መልዕክት ገልጸዋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳም። ምላሽ እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም የድሮን ጥቃት በተመለከተ በሰጣቸው ምላሾች፤ መንግሥት በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰላማዊ ሰዎች ኢላማ እንደማያደርግ ማስታወቁ ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply