“የተራራቀ ትውልድ” ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና
የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)
የሰው ልጅ እርስ በርሱ በማይነጣጠልና ሊነጣጠል በማይችል ባሕሪያዊና ጠባያዊ መገለጫዎች የተሳሰረ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ የሰው ልጅ ከመሰሉ ጋር በሚያደርገው ተፈጥሯዊ ግንኙነት ይወለዳል፡፡ ይወልዳል፡፡ ይባዛል፡፡ አንደኛው ትውልድ ሌላኛውን ትውልድ እንደሚያፈራው ኹሉ እርሱም በተራው ሌላ ትውልድን ያፈራል፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር እንደተሳሰረው ኹሉ ሌላኛውም ከርሱ ጋር ይስተሳሰራል፡፡ በአንድ የዘመን ቀመር ውስጥ ብቻ ያሉ ሳይኾኑ በየዘመናቱ የተራራቁ የሚያስተሳስራቸው ገመድ እስካለ ድረስ ተሳስረው ይኖራሉ፡፡
ይህ በነጠላ ለሰው ልጆች በሙሉ የሚያገለግል ሂደት ዘመኑ በሚጠይቀው ሀገርና ሀገራዊ ማንነት ውስጥም ቢኾን የነበረ – ያለና የሚኖር ተርዕዮ ነው፡፡ ሀገር – ሀገር ትባል ዘንድ ያስቻሏት – በባለቤትነት ስሜት የያዟት – የታሪካቸው አካል ያደረጓት – የታሪኳ አካል ያደረገቻቸው – እሷ እነሱን – እነሱ እሷን መገለጫቸው ያደረጉ ትውልዶች አሏት፡፡
በማንኛውም የሰው ልጅ የሰውነት ክፍል ውስጥ ሕይወት ኖሮት እንዲንቀሳቀስ የደም ስሮች ግንኙነት ትልቁን ድርሻ እንደሚጫወት ኹሉ ሀገርም የትውልዶቿ መስተሳስር መሰረቷ ናቸው፡፡ ይህም የትውልዶች መስተሳስር በዋናነት በሶስት ይከፈላል፡፡
አንደኛ፡- ያለፉ ትውልዶች፤
ሁለተኛ፡- ያሉ ትውልዶች፤
ሶስተኛ፡- የሚመጡ ትውልዶች፤
ሀገር ያለፉ፣ ያሉና የሚኖሩ ትውልዶች እንዳሏት ኹሉ ትውልዶችም የኔ የሚሉት በጋራ የሚጋሩትን ማንነት በሀገር ውስጥ ያገኛሉ፡፡ ሀገር የትውልዶች ውህደት ውጤት ናት፡፡ ሀገር የትውልድ ቅብብሎሽ ሰንሰለት ናት፡፡ ሀገር በትውልዶች ታሪክ፣ በትውልዶች አኗኗርና በትውልዶች ተስፋ ውስጥ ትታያለች፡፡ ትውልዶች በሀገር ውስጥ ሕልው እንደሚኾኑት ኹሉ ሀገርም ሕልውናዋ በትውልዶች ኹለንተናዊ ትግል ላይ ይመሰረታል፡፡
እነዚህ እርስ በራሳቸው የማይነጣጠሉ አንዱ ለብቻው የራሱ መገለጫዎች እንዳሉት ኹሉ አንዱ ከሌላኛው የወሰደውና የወረሰው ብሎም የሚያስተሳስረው ብዙ ነገር መኖሩን ከተለያዩ የታሪክ አሻራዎች፣ ከታሪክ ድርሳናትና ራሱን ከሚተረጉምበት ዐውድ መረዳት ይቻላል፡፡
የአንድ ሰው ማንነት ከመጣበት፣ ካለፈበት፣ ካለበትና ከሚኖርበት ኹለንተናዊ ነገሮች አንጻር በጥምረት እንደሚታይ ኹሉ የአንድ ሀገር ማንነትም ትውልዶቿ ከመጡበት፣ ካለፉበት፣ ካሉበትና ከሚኖሩበት ኹለንተናዊ ዕውነታዎች (REALITIES) እና ዕውነቶች (TRUTH’S) የሚመነጭ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡
እርስ በራሱ የሚያደርጋቸው ኹለንተናዊ የፍላጎት ግንኙነቶች – ጊዜና ወቅቱ በሚጠይቀው ኹለንተናዊ መስተጋብር በመንፈስ የሚግባባ፣ በልቡ የሚተማመን፣ በአዕምሮው በየጊዜው የሚያድግ እና ዘወትር አንዱ በሌላኛው – ሌላኛው በአንደኛው ውስጥ የሚኖር ትውልድ ታላቅ ታሪክ ከመስራት በላይ ለሀገር ኩራት – ለወገን አለኝታና ለትውልዶችም መከበሪያ እንደሚኾን የአደባባይ ዕውነታ (REALITY) እና ዕውነት (TRUTH) ስለመኾኑ አያጠራጥርም፡፡
ታድያ እኛ እንደሀገር ምን ላይ ነን? እርስ በርሱ በመሠረታዊ ሀገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያልተራራቀ ትውልድ አለን? ይህ ሳይኖረን እንደምን ልንሠለጥንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ልንኾን እንችላለን?
በሀገራችን መሬት ላይ ያለውን ጥሬ ሃቅ ስንመለከት ትውልዱ እጅጉን ተራርቆ ብቻ ሳይኾን እጅጉን በተቃርኖ ውስጥ እንደሚኖር አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡ ይህንንም ከተለያዩ ማዕቀፎች አንጻር መመልከት ይቻላል፡፡
ይኸውም፡-
1. ከጊዜ ማዕቀፍ አንጻር፤
 ትውልዱ ተራርቆ ያለበት የዕይታ (Perspectives) ልዩነት ከጊዜ ማዕቀፍ አንጻር በሶስት የሚከፈል ነው፡፡
I. ከትላንት
– እንደሀገር ትውልዱ ትላንትን በሚያይበት፣ በሚተነትንበትና ቦታ በሚሰጥበት ሂደት ላይ ያለው መራራቅ እጅጉን የሰፋ – ሀገር እያለው ከሀገር በታች በመንደርና በከባብያዊነት የተጥለቀለቀ – የጋራ ትላንት ቢኖረውም በተናጠል ትላንት ውስጥ መወሸቅን ብሎም ከመወሸቅ ባሻገር “አትድረሱብኝ” – “አልደርስባችሁም” አይነት ምልከታን የሚያሳይ ኾኖ ይገኛል፡፡
II. ከዛሬ
– ትውልዱ ሀገሩ ዛሬ ስላለችበት ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹኔታዎች እጅጉን የተራራቀና ሊቀራረቡ የሚችሉበትም ኹኔታዎች በእጅጉ የሚያስፈሩ እሰጣ ገባዎች፣ መቧደኖች፣ መጠላለፎች፣ ጥላቻዎች፣ እጅጉን የታጠሩና ‘የኔ’ – ‘የኔ’ የበዛባቸው በርካታ ኹነቶችን መመልከት የዕለት ተዕለት ተርዕዮ ነው፡፡
III. ከነገ
 ትውልዱ ስለሀገሩ ኹለንተናዊ የነገ ኹኔታዎች የጋራ የኾነ መሠረታዊ መግባባት እንደሌላው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
 እንደሀገር ስላለንበት ብቻ ሳይኾን ልንኾን በምንፈልገው ኹለንተናዊ የነገና የከነገ ወዲያ ፍላጎቶች ላይ ያለው መራራቅ እጅጉን አሳዛኝ፣ አስፈሪ ብሎም አለፍ ሲል አሳፋሪም ጭምር ነው፡፡
 ለዚህ መገለጫ የሚኾኑ በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም የማሕበራዊ ሚድያ እሰጣ ገባዎች፣ የሚድያዎች (ጋዜጣዎች፣ መጽሔቶች፣ ቴሌቭዥንና ሬድዮ ፕሮግራሞች)፣ የገዥዎች ያልታረሙ አንደበቶች – – – ወዘተ የሚነዟቸው ወሬዎች፣ ንግግሮችና መግለጫዎች ማሳያ ናቸው፡፡
2. የጋራ ሀገራዊና ሕዝባዊ ዕሳቤን ከመያዝ አንጻር፤
እንኳንስ ትውልድ እንደትውልድ ይቅርና ነጠላ ግለሰብ ከሌላኛው ግለሰብ እጅግ የተለየ ኹለንተናዊ ሀሳብና ዕሳቤ ሊኖረው እንደሚችልና – እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ኾኖም ግን ሀገር የነዚህ መግባባት የቻሉም ኾነ ያልቻሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ተቋማት ጥምረት ናትና – የጋራ ስለኾነች ሀገር ቢያንስ በጋራ ጉዳያቸው ላይ – የጋራ ዕሳቤ መያዝን የግድ ይላል፡፡
በጋራ ጉዳይ ላይ የጋራ ዕሳቤን መያዝ – የጋራ ባለቤትነት ማረጋገጫ ጭምር ቢኾንም ትውልዱ በጋራ ጉዳይ ላይ የተናጠል ጉዳዮችን እንዳሠለጠነ – ከዚህም አልፎ በጋራ ላይ የተናጠል ፍላጎትና ጥቅሞችን ለመጫን በሚያደርገው ኹለንተናዊ ግልጽና ስውር፣ መደበኛና መደበኛ ያልኾኑ ኹለንተናዊ ጥረቶች ውስጥ ያሉ “ኹለንተናዊ ትውልዳዊ ጦርነቶች” የዚህ ማረጋገጫ ናቸው፡፡
እንደትውልድ ትውልዱ በተግባር በተጨባጭ የጋራ ያደረጋቸው ነገሮች ምን አሉ? ከመራራቅ በዘለለ መራራቁ ወደ መለያየት እንዳያመራ ያስተሳሰረው ገመድ አልያም የሚያስገድደው የጋራ ዕሴት ምን አለው? ትውልዱ የኔ የሚላቸው የመራራቁ ፊት አውራሪ ነጅዎች እንዳሉት ኹሉ የጋራ ገዥ እንጂ የጋራ መሪ ማን አለው? ዕውን ትውልዱ መሪ አለው ብሎ አፉን ሞልቶ የሚናገር ማን ነው?
እስኪ ትውልዱን የሚያስተሳስር፣ የሚያቀራርብና በኹሉም ትውልድ ዘንድ ሊደመጥ የሚችል ሀገራዊ መሪ ማን አለን? ገዥያቸው አልያም መሪዪ ከማለት ዘለን መሪያችን ያልነው ማን አለን? ከመለያየት ይልቅ የማቀራረብ ሥራ የሚሰራ፤ ከሴራና ከማስመሰል የራቀ፤ ከማንም የግለሰብ፣ ቡድን ኾነ ተቋም አሽከርነትና ገረድነት ነጻ ወጥቶ በዕሳቤና በሀገራዊ ርዕዮት ትውልዱን የሚመራ፤ በተራ ፍሬ ከርስኪ የአደባባይ ድራማዎች ያልታጠረ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ የኮስሞቲክስ ፖለቲካ ያልተዋጠ፤ ከራሱ አልያም ከቡድናዊ ፍላጎት በላይ የሀገርና ሕዝብ ፍላጎትን ያሠለጠነ – ትውልዶችን ከማራራቅ ፈጽሞ የጸዳ – ትውልዶችን ማቀራረብ የቻለ ማን ነው?
ከማስመሰል፣ ከተራ ከፋፋይ ንግግሮች የራቀ፣ ራሱን ማረምና ራሱን መጠበቁን አንደበቱን በማረም የሚተጋ – ከአደባባይ ሕዝባዊና ሀገራዊ ውሸቶች የራቀ – የትውልዱ አርዓያ ማን ነው? ያለ ልዩነት በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅ ኾነ በማዕከል ያለ ትውልድን ለማቀራረብ ሌት ተቀን የሚተጋ – ከስሜት ይልቅ በዕውቀት፤ ከአስተያየት ይልቅ በዕሳቤ፤ ከችኮላ ይልቅ በትዕግስት፤ ከሴራ ይልቅ በጥበብ፤ ከአሉባልታና ከፍሬ ከርስኪ ትርጉም አልባ የቃላት ድርደራ ፈቀቅ ብሎ በርዕዮተ ዓለም (በተለይ ርዕዮተ ሀገር) ላይ ትኩረት አድርጎ የሚተጋና የሚያተጋ፤ ከትላንት ዕይታ ይልቅ ነገን ማዕከል አድርጎ ዛሬ ላይ ጠንክሮ የሚሰራ – ሙሉ አቅም ያለው – የትውልዱ አለኝታ ማን ነው? ይህ የሌለው ትውልድ ቢራራቅ ምን ይገርማል? እንዲህ ያለ ትውልድ ያልተራራቀ – ማን ይራራቃል?
3. ከዕምነት፣ ከዕውቀትና ከድርጊት ማዕቀፍ አንጻር፤
በአንድ ሀገር ውስጥ ግለሰባዊ፣ ቡድናዊና ተቋማዊ ኹለንተናዊ ልዩነቶች ባሕሪያዊና ጠባያዊ ህልው ዕውነታዎች ቢኾኑም የጋራ ሀገር አለኝ የሚል ትውልድ ቢያንስ ቢያንስ በመሠረታዊ የጋራ ሀገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከመጣበት፣ ካለፈበት፣ ካለበትና ከሚኖርበት (መኖር ከሚሻው) አንጻር የጋራ የሚለው የሚያቀራርበው፣ የሚያስተሳስረው፣ በጋራ ባለቤትነት የሚይዘውና የሚያሻግረው – ከሌሎች መሰል ሀገራትና ሕዝቦች አንጻር “እኔ እንዲህ ነኝ” ብሎ ትርጓሜ መስጠት፣ ማነጻጸርና ማመላከት የሚያስችለው የጋራ መግባባት ይኖረው ዘንድ ግድ ይላል፡፡
እንደግለሰብ፣ እንደቡድንና እንደተቋም ትውልዱ ትርጉም ባለው መንገድ በሀገራዊና ሕዝባዊ ኹለንተናዊ ጉዳዮች በዕምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (በስልትና ስትራቴጂ) እና በድርጊት (በተግባር) ደረጃ እጅጉን እንደተራራቀ ማንም የማይክደው ጥሬ ሃቅ ነው፡፡
የተራራቀ ትውልድ በምንም መንገድ ካልተራራቀ ትውልድ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር ብሎም በአሸናፊነት ሊወጣ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ የተራራቀ ትውልድን የያዘች ሀገር ከወደፊት ይልቅ ወደ ኃላ፤ ከዕድገት ይልቅ በዝቅጠት፤ ከክብረት ይልቅ በውርደት፤ ከሥልጣኔ ይልቅ ስይጥንና፤ ከከፍታ ይልቅ ዝቅታ ውስጥ ከመገኘቷም በላይ ስሜት (Emotion)፣ አስተያየት (Opinion)፣ ሀሳብ (Idea)፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት ዓለም /ርዕዮተ ሀገር/ (Ideology) በአንድ ሀገር ኹለንተናዊ ያለፈ፣ ያለና የሚኖር እንቅስቃሴ ውስጥ የማይነጣጠል፣ ተያያዥና ተደጋጋፊ ሚና ያላቸው ቢኾንም በስሜት (Emotion) እና በአስተያየት (Opinion) የምትገዛ ሀገር እንደምትኾን – አርቴፊሻልና የማስመሰል ሥራዎች እንደሚበራከቱባት! ሴረኛነት እንደጥበብ ተቆጥሮ እንደሚከበርባት! ከኹሉ ጭራ እንደምትኾን! ዘወትር ለተከታይነት እንደምትሰራ! ባርነት እንደነጻነት ባደባባይ የሚሰበክባት እንደምትኾን! የአደባባይ የኮስሞቲክስ ተራ ትርጉም አልባ የፖለቲካ ትያትር እንደሚሠለጥንባት ታሪክ ብቻ ሳይኾን አኗኗራችንም ጭምር ምስክር ነው፡፡
ከላይ በተገለጹ እጅግ በጣም በተወሰኑ ማዕቀፋዊ መገለጫዎች እንደተመለከትነው ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ በሚጥል ኹኔታ – ከሀገራዊና ሕዝባዊ ዕይታዎች አንጻር ትውልዱ እንደተራራቀ – ሀገራችን የተራራቁ ትውልዶች መኖሪያ መኾኗን ማንም የማይክደው ጥሬ የአደባባይ ሃቅ (Fact) ነው፡፡
ይህ ትውልድ እንደተራራቀ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኃላ ቀጣዩ ጥያቄ ምን አራራቀው? በዚህ መራራቅ ውስጥ እነማን – ምን ሚና አላቸው? ለምን? መንሥኤው ምንድነው? የሚለውን ትርጉም ባለው መንገድ በጥልቀትና በስፋት ከኹለንተናዊ አቅጣጫ መርምሮ ለማቀራረብ ምን ሊደረግ ይገባል? በማቀራረብ ሂደትስ – ከማን ምን ይጠበቃል? የሚለውን መመልከት ኹነኛ ብቸኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡
በሀገራችን ካለፉ ትውልዶች ኾነ ካሉ ትውልዶች ኹለንተናዊ መራራቅ በላይ የሚቀጥለው ትውልድ መራራቅ እጅግ አስፈሪ ብቻ ሳይኾን ሀገራዊ ሕልውናን ጭምር የሚፈታተን ብሎም ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ በመኾኑ ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ትውልዳዊ ኃላፊነት ከመኾን ባሻገር ትውልዳዊ ግዴታም ጭምር ነው፡፡
የተራራቀ ትውልድ ታሪክ ይሰራበታል እንጂ ፈጽሞ ታሪክ ሰርቶ አያውቅም፡፡ የተራራቀ ትውልድ የተራ ትርጉም አልባ አሻንጉሊቶችና ገረዶች ኹለንተናዊ ፍላጎቶች መጫወቻ ይኾናል እንጂ የራሴ የሚል ታሪክ አይኖረውም፡፡ ያልተራራቀ ትውልድ በሥልጣኔ ጎዳና ሲራመድ – የተራራቀ ትውልድ በአንጻሩ በስይጥንና መኖርን ገንዘቡ ያደርጋል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!
ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply