የተቀሸበና በሲር የተሰፋ የግብዓት ስርጭትና የአርሶ አደሩ እሮሮ! ባህርዳር:- ሚያዚያ 29/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ በሳን…

የተቀሸበና በሲር የተሰፋ የግብዓት ስርጭትና የአርሶ አደሩ እሮሮ! ባህርዳር:- ሚያዚያ 29/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ በሳንክራ ከተማ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር በከረመ 1ሺህ 2መቶ 65 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ላይ የቅሸባና ተለያዩ ድርጊቶች በመፈፀማቸው የግብዓት እጥረቱንና ስርጭቱን ከማስተጓጎል ባለፈ ለተለያዩ እንግልቶች እየተዳረጉ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ የሳንክራ ገነታ ቀበሌ ነዋሪ ወታደር ከፋለ አብዪ እንደተናገሩት አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ለማውጣት 4ሺህ 1መቶ 50 ብር ከፍለን ወደመካዝን ስንገባ የከረመው ግብዓት ተቀሽቦና በሲር ተሰፍቶ እንዲሁም የኪሎ መጠኑ ከ20 እስከ 35 ኪሎ ግራም ወርዶ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡በተለያዩ የሀሳብ አውታሮች በተወጠርንበት እና ወደ እርሻችን ለመመለስ በጓጓንበት በዚህ ወቅት ይህ አይነት ድርጊት መፈፀሙ ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ሆኖብናል፡፡ አንዲት ከረጢት በፋብሪካው የተሰፋች ማዳበሪያ ለማግኘትም ከ15 እስከ 20ና በላይ ኩንታል የጎደለ፤ በሲር የተሰፋ፤ ባዕድ ነገር የተቀላቀለበትና የተቀሸበውን በአዲስ መልክ ወደሌላ ቦታ ገልብጠን መደርደር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ወረዳው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብዓት ለማዳረስና እጥረቱን ለመቅረፍ በሚንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት ጥቂት ስግብግብ ወገኖቻችን በጉሮሮአችን ላይ እንጨት በመላክ መንግስትንና ህዝብን ሆድና ጀርባ ለማድረግ ታልሞ የተሰራ ሴራ መሆኑን የሚገልፁት ደግሞ አርሶ አደር ደመቀ መላክና ጥላሁን አንዱዓለም ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም በህብረት ስራ ማህበሩ ላይ እምነት እንድናጣ ስራዎች እየተሰሩብን ስለሆነ መንግስት በአጥፊዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ በግብዓት እጥረት እንዳንጉላላ በአዲስ የድልደላና የስርጭት ስራ እንዲሰራላቸው አሳስበዋል፡፡ የሳንክራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር የቁጥጥር ኃላፊ አቶ ሰጠኝ ደመላሽ በበኩላቸው የግብዓት ቆጠራና የስፌት ስርዓቱ ሲካሄድ የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ ወደ ግንባር መሔዳቸውን ጠቁመው ከጉድለቱ በተጨማሪ ለሰፊና ለደርዳሪ በሚል ሂሳብ መወራረዱን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን የግብዓት ቆጠራ እና ኦዲት ሲደረግ በደንብ ከመመርመር ባለፈ ቁመው ያሰፉትና ያስደረደሩት አካላት ጥቆማውን ለኦዲተሮች የማሳወቅና በጉድለት እንዲያዝ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነበረብን ብለዋል፡፡ በቀጣይ ግን አዲስ ኦዲተር ገብቶ እንደገና እንዲቆጠርና ወንጀለኛውን ተጠያቂ በማድረግ አርሶ አደሩን መካስ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወረዳው ህብረት ስራ ማህበራት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ስሜነህ በበኩላቸው ተቋሙ 2እና 3 ዓመታት በተለያዩ ተወካዮች መመራቱ በሁሉም የገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበራት ላይ የተለያዩ ችግሮች መንሰራፋት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በሳንክራ ገነታ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር 1ሺህ 2መቶ 65 ኩንታል የከረመ ማዳበሪያ ለግብዓት ለወረዳ መረጃ በመስጠት ለግብዓት ቆጠራ ባለሙያዎችና ለኦዲተሮች ቂጡን ባዶ በማድረግ ወደ ጫፉ በመሙላት ለቆጠራ በሚመች መልኩ በተጠና አካሔድ በመደርደሩ ጉድለቱና ችግሩ በቀን 27/08/2014ዓ.ም በስርጭት ወቅት አርሶ አደሮችን በተራ አውጡ በሚልና የጎደለና በሲር የተሰፋ ማዳበሪያ አናወጣም በሚል ግብግብና ጠቆማ ጠቅላላ ችግሩ እንዲጋለጥ አድርገዋል፡፡ የተከሰተው ችግርም ወረዳው ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር መንስኤ እንዲገጥመው ከማድረግ ባሻገር አርሶ አደሩ በወቅቱ ሰብሉን እንዳይዘራ ለማስቻል ነው፡፡ ተቋማቸውም ከአርሶ አደሩ በተሰጣቸው ጥቆማ መሰረት በፍጥነት ወደሁለገቡ የህብረት ስራ ማህበሩ በማምራት አርሶ አደሩ እንዳይጉላላ እየመረጠና አዲስ ከገባው እንዲወስድ ጥረት አድርገናል ብለዋል፡፡ የችግሩ ምንስኤ አካለትንም የተለያዩ አመላካች መረጃዎችን ከመሰብሰብ ባለፈ ወረዳው የችግሩን ስፋት ተመልክቶ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድና በአዲስ መልክ ኦዲት እንደሚያስደርጉም ገልፀዋል፡፡ ውድ የድህረገፃችን ተከታታዪች የቀጣይ ድርጊቶችን ተከታትለን መረጃ እናደርሳል፡፡ #ሰ/አቸፈር ኮሙዩኒኬሽን ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 youtube :- https://www.youtube.com/channel/UChir2nIy58hlLQRYyHIQeHA

Source: Link to the Post

Leave a Reply