የተቃውሞ ሰልፈኞች እና የጸጥታ ኃይሎች ግጭት በሶማሊላንድ

https://gdb.voanews.com/D3697601-B6F5-4326-926C-FCFF6516A08E_w800_h450.png

በተገንጣዩዋ ሶማሊላንድ ተቃዋሚ ቡድኖች እና የፀጥታ ኃይሎች መጋጨታቸው ተዘግቧል። አንድ የሶማሊላንድ የሰብዐዊ መብት ቡድን መሪ እንዳሉት በግጭቱ ቢያንስ አንድ ሰው ተገድሏል። 

ከሶማሊያ በተገነጠለችው በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ውስጥ ዛሬ ሐሙስ በተቃዋሚ ሰልፈኞች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ብዛት ያላቸው ሰዎች ተጎድተዋል።

የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን የሚቃወሙ መፈክሮች ያሰሙ በነበሩት እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው መዘግየቱን በተቃዋሙ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ጥይት መተኮሳቸው ተገልጿል።

ሀርጌሳ የሚገኝ የሰብዐዊ መብት ቡድን መሪው አህመድ ዩሱፍ ሁሴን ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ በሰጡት ቃል “በግጭቱ የተገደለ አንድ ሰው እንዲሁም አስራ አምስት ቁስለኞች አይቻለሁ” ብለዋል።

“የተቃውሞ ሰልፉ ላይ የነበሩት ሰዎች፣ በተለይም ወጣቶቹ ወንዶች እና ሴቶች ጎዳናዎችን አጥረው ስለነበረ ፖሊሶቹ ሊበትኗቸው የዕውነት ጥይት ተኮሱባቸው” ብለዋል። ቁስለኞቹ ወደሆስፒታሎች መወሰዳቸውን ሰምቻለሁ ያሉት አህመድ ዩሱፍ ራሴም ዕድሜው ከሃያ ስምንት እስከ ሠላሳ ዐመት የሚሆን የተገደለ ወጣት እና ዘጠኝ ቁስለኞችን አይቻለሁ፣ ሦስቱ ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ዩሲድ በሚል የእንግሊዝኛ ምህጻር የሚጠራው የሶማሊላንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፈይሰል አሊ ዋራቤ በበኩላቸው፣

“የፀጥታ ኃይሎቹ በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ ባካሄዱት ተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተመለባት ጥቃት አድርሰውባቸዋል” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። አሁን ያለው አስተዳደር ምርጫው እንዲካሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሪፐብሊኳን መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ከትቷታል ሲሉም አክለዋል። የምክር ቤቱ አባላት የሥልጣን ዘመን አብቅቷል፣ የፕሬዚዳንቱም የሥልጣን ዘመን በመጪው ህዳር ውስጥ ያበቃል” ብለዋል።

“ብዙ እንስሳት ባለቁበት ድርቅ እና በዋጋ ንረት መሃል ባለንበት በዚህ ወቅት ለተቃውሞ ሰልፍ እንድንወጣ መገደዳችን ያሳዝነናል” ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ሰልፈኞቹ ፖሊሶቹን በመጋፈጥ ያደረጉት ነገር አልነበረም ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ የጸጥታ ኃይሎቻቸውን ልከው ተኩስ አስከፍተውባቸዋል” ብለዋል። ሶማሊላንድ ከዚህ የከፋ ቀን አጋጥሟት አያውቅም በማለትም አክለው ተናግረዋል።

የአሜሪካ ድምፅ የሶማሊላንድ የማስታወቂያ ሚንስትርን እና የገዢውን የኩልሚዬ ፓርቲን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ሞቃዲሾ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሶማሊላንድ ገዢዎች እና የተቃዋሚ መሪዎች ከሁከት ተቆጥበው በአስቸኳይ ወደ ፖለቲካ ንግግር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል። አያይዞም ኤምባሲው ምርጫዎቹን በሚመለከት ሥምምነት ላይ ለመድረስ ካልቻሉ ሶማሊላንድ እስካሁን ባስመዘገበቻቸው የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ክንዋኔዎቿ ላይ አደጋ ይጋርጣል በማለት አሳስቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply