የተቋሙን ውስጣዊ የአሰራር ሥርዓቶች በማስተካከል ተወዳዳሪና ደንበኞች የሚረኩበት ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለአገልግሎት አሰጣጡ የማይመቹ ውስጣዊ የአሰራር ሥርዓቶችን በመፈተሽና ጠንካራ ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ተወዳዳሪና ደንበኞች የሚረኩበት ተቋም ማድረግ እንደሚገባ አዲሱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል፡፡

የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዋ ይህንን የገለፁት ሐምሌ 23 ቀን 2014 የተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለደንበኞቹ መስጠት የተቋሙ ዋና ሃላፊነት ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ ውስጣዊ የአሰራር ክፍተቶችን መሙላትና የአገልግሎት አሰጣጡን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚተገበሩ ቴክኖሎጂዎችን ሊሸከም የሚችል የሰው ሃይል መገንባትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የገለፁት ፍሬህይወት፤ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራም እንዲሁ የተለየ ትኩረት የሚሹ የሥራ ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዋ አክለውም ተቋማዊ የኢንዱስትሪ ሰላም በመፍጠር እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት መሸከም የሚችል የሰው ሃይል በመገንባት የደንበኞችን የእርካታ ደረጃ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አስቀድመው የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን በማስቀጠል የተቋሙ ስትራቴጂ ዳግም በመፈተሽና የትኩረት መስኮቹን በአግባቡ በመለየት እንዲሁም በስራ ሂደት የታዩ ውስንነቶች በመቅረፍ ተወዳዳሪና ገጽታው የተገነባ ተቋም የመገንባት ሂደት እውን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም በየደረጃው ያለው አመራርና ፈፃሚ ደንበኞችን በማህበራዊና ኢኮሚያዊ ልማት መስክ በሚያመጡት ፋይዳ ልክ በመለየት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ማገልገል እንደሚገባ፣ የተቋሙን የገቢ ምንጮች ማስፋት አንዲሁም ከገንዘብ አሰባሰብ ስርዓቱ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመቅረፍ የተቋሙን ገቢ ማሳደግና ተቋሙ ያለበትን የፋይናንስ ዕጥረት መቅረፍ ይገባል ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply