የተከዘ ግድብ የአየር ጥቃት ደረሰበት ተባለ

የፌደራል መንግስት ተዋጊ ጀቶች የተከዘ ሃይል ማመንጫ ግድብን እንደደበደቡ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የዜና ወኪሉ ባለፈው ሳምንት ሑመራ ያጠቁ ወታደሮች በኤርትራ በኩል የመጡ መሆናቸውን ተሰደው ሱዳን የሚገኙትን የአይን እማኞች በመጥቀስ በዘገባው አስፍሯል።

አሶሼትድ ፕሬስ ዶ/ር ደብረፅዮን እንዳሉትና በክልሉ ቲቪ እንደቀረበው ብሎ እንደዘገበው የፌደራል መንግስት የራሱ የሆነውን የተከዘ ሀይል ማመንጫ ግድብ በጦር አውሮፕላ ደብድቧል። ፌደራል መንግስት በትግራይ ላይ ‘’ህግ የማስከበር ኦፕሬሽን’’ ብሎ በጠራው የጦርነት አዋጅ መሰረት የመብራት፣ የስልክ፣ የባንክ እና ኢንተርኔት አግልግሎቶች በክልሉ እንዲቋረጡ አድርጓል። ነገር ግን ክልሉ ከተከዘ ሃይል ማመንጫ ኤሌክትሪክ በመጥለፍ ለመጠቀም ጀምሮ ነበር። የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎትም ከፌደራል ውጪ ለማግኘት ሙከራ ላይ መሆኑን የክልሉ ሰዎች ከሰሞኑ ሲናገሩ ተሰምቷል።

ይህን ያወቀ የፌደራል መንግስት በክልሉ የመብራህት አገልግሎት እንዳይኖር በማሰብ በግድቡ ላይ ድብደባ መፈጸሙን ዘገባው ያስታውሳል።
ለእርስ በርስ ጦርነት ያጋደለ ውግያ እየተካሄደ ነው ያለው ዘገባው፣ ይህንን ሊመጣ እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩ የህወሓት ከማእከላይ መንግስት መገለል እንዳምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳል።

ትግራይ ከሁሉም አገልግሎቶች ውጪ ስለሆነች መረጃ ለማጣራት እና ለተጎጂዎች እርዳታ ለማድረስ አስቸጋሪ እንደሆነ ዘገባው ይገልፃል። እስካሁን በጦርነቱ ተፈናቅለው ወደ ሱዳን የሸሹ ኢትዮጵያውያን ሰዎች ብዛት 11 ሺ እንደደረሰ፣ በአጠቃላይ ደግሞ አንድ መቶ ሺ ስደተኛ ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል።

ይህ የኤርትራ መንግስት ጭምር እየተሳተፈበት ያለ መሆኑን የተወሳው ጦርነት፣ ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በላይ እንዳይዛመት ፍርሃት አለ ሲል ዘገባው ያክላል። በተለያዩ ቦታዎች የሽብር ጥቃት ለማድረስ ተያዙ የሚባሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ፣ በአዲስ አበባ ብቻ ትላንት ሓሙስ 242 ሰዎች እንደተያዙ ፖሊስ አስታውቋል።

መንግስት ከሁሉም ብሄርብሄረሰብ የተገኙ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ይዣለሁ ቢልም በብዛት ግን የትግራይ ተወላጆችን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply