“የተከዜን ድልድይ አፍርሰውታል፣ ክፉውን ሁሉ አድርገውታል”! ጳጉሜ 03/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) እልፍ ነብሶች በእጁ አልፈዋል፣ ሀገሬን ያሉትን ገድሏቸዋል፣ ኢትዮጵያን የጠሩት ሞተዋል…

“የተከዜን ድልድይ አፍርሰውታል፣ ክፉውን ሁሉ አድርገውታል”! ጳጉሜ 03/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) እልፍ ነብሶች በእጁ አልፈዋል፣ ሀገሬን ያሉትን ገድሏቸዋል፣ ኢትዮጵያን የጠሩት ሞተዋል፣ ሠንደቋን ከፍ ከፍ ያደረጉት ላይገኙ ጠፍተዋል። ያፈሰሳቸው ደሞች፣ ያጠፋቸው ጀግኖች፣ የሠወራቸው የታሪክ አዋቂዎች ብዙ ናቸው። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ያልፈፀሙት፣ ያላደረጉት የት ተገኝቶ? በክፉ እጆቻቸው ደም እንደ ቦይ ፈስሷል፣ አጥንት ተከስክሷል፣ ሰውነት ረክሷል፣ ከምንም ነገር አንሷል። ኢትዮጵያን ለማሳነስ፣ የፀናው ሀገራዊ አንድነቷን ለማፍረስ ከየትኛውም ጠላት ጋር ይወዳጃሉ፣ ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ታሪካዊ ጠላታቸው ፣ ኢትዮጵያን የሚጠላ ሁሉ የልብ ወዳጃቸው ነው። ዓመታትን ባስቆጠረው ዘመኑ በጨካኝ እጆቹ እልፍ ነብሶች ታንቀው ሞተዋል፣ እልፍ ነብሶች ቀ…ባሪ አልባ ቀርተዋል፣ እልፍ ነብሶች ማንም በማይሰማበት ድቅድቅ ጨለማ እየጮኹ ለዘለዓለም አሸልበዋል፣ በዱር በገደል ተጥለው የአራዊት እራት ኾነዋል፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ተለቅሶ መቀበር ብርቅ እስኪኾን ድረስ ቀባሪ ሳይጠራላቸው፣ ቀብር አስፈፃሚ ሳይቀብራቸው፣ ወገን እና ዘመድ ሳይዳብሳቸው፣ ዳብሶ ሳይገንዛቸው፣ ነብስ ይማር ብሎ አፈር ሳያለብሳቸው ድንገት የቀሩት ብዙዎች ናቸው። ባለ ቤቶችን ቤት አልባ አድርገዋቸዋል፣ ባለ እርስቶችን እርስት የለሽ ባተሌ እንዲኾኑ ፈርደውባቸዋል፣ እየተከታተሉ ምድርን እስኪጠሏት፣ ሞትን እስኪናፍቋት ስቃይ አብዝተውባቸዋል። የጨለማ ቤቶቻቸው የመከራ ድምጽ ይሰማባቸዋል፣ ተውኝ የሚሉ የንፁሐን ድምፅ ይስተጋባባቸዋል፣ ታዲያ በእነዚያ የመከራ ቤቶች፣ የስቃይ መናኸሪያዎች ምሕረት የለም። የሚጮኹትን እያሰቃዩ ይገድሏቸዋል፣ ከስቃይ ላይ ስቃይ ያደርሱባቸዋል፣ ስጋቸው እንዳታርፍ አውጥተው ይጥሏቸዋል። በንፁሐን እንባ ይስቃሉ፣ በደካሞች ለቅሶ ሃሴትን ያደርጋሉ። ደስታቸው በንፁሐን ሀዘን ላይ የተመሠረተ ነውና ንፁሐን በሳቁ ጊዜ ያለቅሳሉ፣ ንፁሐን በተደሰቱ ጊዜ ይከፋሉ፣ ወንድማማቾች በተዋደዱ ጊዜ ሰላም ያጣሉ፣ ወንድማማቾች ሲለያዩ፣ እንደባላንጣ ሲተያዩ ደስታቸው እጥፍ ይኾናል። ከወንድማማቾች ጠብ ያተርፋሉ፣ ከመለያየት ንዋይ ይሰበስባሉ ፣ ደስታ ያገኛሉ እና በተጣሉላቸው ጊዜ ደስ ይላቸዋል። በተዋደዱም ጊዜ ይከፋቸዋል። ብዙዎች ጨለማ በበዛበት፣ አራዊት በሚመላለሱበት፣ የራሳቸው ግዛት ባደረጉት ጫካ ውስጥ እጅ እግራቸው ተጠፍሮ ተጥለዋል፣ ዓይናቸው እያየ የሚያድናቸውን እየተማፀኑ በአውሬ ተበልተዋል። በደል ሳይኖርባቸው በደል የተቆጠረባቸው፣ ሀጥያት ሳይገኝባቸው ሞት የተፈረደባቸው፣ መኖር ሲመኙ እድሜያቸው በጨካኝ እጆች የተቆረጠባቸው ነብሶች እየተሰቃዩ አሸልበዋል፣ መኖር እየናፈቁ ጠፍተዋል፣ መውለድ መክበድ እያለሙ በክፉ እጆች ተረሽነው ቀርተዋል። የኢትዮጵያ እናት አልቅሳለች፣ እንባውን እየጠረገች ለዓመታት ኖራለች። ለምን ካሉ ልጇ በወጣው ቀርቷል፣ ይጦረኛል ብላ ዓይን ዓይን ስታየው ሞቷል፣ ሳይሰናበታት ለዘላለም ተሰናብቷልና ለዘመናት አምርራ አልቅሳለች። ጎንጮቿ የእንባ ዘለላዎች ያለ ማቋረጥ እየፈሰሰባቸው፣ አንጀቷ በስቃይ እያረረባቸው ዓመታትን አሳልፋለች። ኢትዮጵያን የምትወድና ኢትዮጵያውያንም የሚወዱህ ቸሩ አባት ኾይ በቃሽ በለኝ፣ የመከራውን ዘመን አሳልፍልኝ፣ ምርኩዜን አትንጠቀኝ፣ ጧሪ አልባ አታስቀረኝ፣ በምድሯ ላይ ተነስተው መከራ የሚያበዙብኝን፣ ከስቃይ ላይ ስቃይ የሚደራርቡብኝን በቃችሁ በላቸው፣ አንተው ቅጣቸው ስትል ኖራለች። ጥቁሩን ልብስ አውልቃ ነጭ መብሩቅ የምታጠልቅበት፣ ጠቢብ ሸማኔ ባሳመረው ቀሚስ የምትዋብበት፣ ሹርባ ተሠርታ የምትገማሸርበት፣ በሀዘን የጨፈገገው ፊቷን አስውባ የምትስቅበት ዘመን ሲናፍቃት ኖሯል። የልጅ ሞት ሰልችቷታልና ደጉን ዘመን ስትናፍቀው ኖራለች። ሰላም ውሎ ማደርን ተመኝታለች። ከሕዝብ፣ ከመንግሥት ፣ ከሃይማኖት ፣ ከእሴት እና ከባሕል ጋር የተጋጨው የሕወሓት የሽብር ቡድን ቢሳካለት ይወራል፣ በወረረው አካባቢ ያገኘውን ይዘርፋል፣ ከዘረፋ የተረፈውን “ባልበላ ጭሬ ላፍሰው” በሚል ብሒል ያወድማል፣ ከሕዝብ ጋር ፀብ የለኝም ብሎ ሲምል ሲገዘት ይታያል፣ ነገር ግን ንፁሐንን ያለ ርህራሄ ይገድላል። አብያተክርስቲያናትን ያወድማል፣ መስጂድ ያረክሳል። የሚጠለሉበት ቤት፣ የሚማፀኑበት፣ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት ማምለኪያ ያሳጣቸዋል። የሕወሓት የሽብር ቡድን ክፉ እጆች በአማራ ምድር አያሌ በደሎችን አድርሰዋል፣ ንፁሐንን በጅምላ ገድለው፣ በጅምላ ቀብረዋል፣ የቀሩትን ያለ ቀባሪ በዱር በገደል ጥለዋል፣ ለዓመታት ያጠራቀሙትን ሃብትና ንብረት ምንም ሳያስቀሩ ዘርፈዋል፣ መነኮሳትን ደፍረዋል፣ እናቶችን ጡት ከሚያጠቧቸው ልጃቸው ለይተው ገድለዋል፣ ሕፃናትን በአስከሬን መካካል በቤት ውስጥ ዘግተዋል።የሚጠሉትን ሕዝብ ያጠፉታል፣ አንገቱን ያስደፉታል፣ ሀገሩን ያስጠሉታል፣ መድረሻ ያሳጡታል፣ ሀገር አልባ ያደርጉታል፣ ያሉትን ሁሉ አድርገዋል። ዳሩ መከራዎች የሚያጠነክሩት፣ ፈተናዎች የሚያፀኑት፣ ችግሮች ሁሉ የማይበግሩት፣ ጀግንነት ፣ ፅናት እና አይበገሬነት ያለው ሕዝብ ነውና ሰበርነው ሲሉት ይሰብራቸዋል፣ አለያየነው ሲሉት አንድ ይኾንባቸዋል፣ ጨረስነው ሲሉት ይበዛባቸዋል። ሃብቱን ዘርፎ፣ ሕይወቱን ነጥቆ አልበቃ ሲለው ታላቁን ድልድይ አፍርሶታል። የሽብር ቡድኑ የሰበረው ድልድይ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ በቆራሪት መሥመር ያለውን ነው። ይህ ድልድይ የአማራና የትግራይ ዜጎች የሚገናኙበት፣ የትግራይና የአማራ ክልሎች የሚዋሰኑበት ነው። ዳግም ወደ ወልቃይት እንደማይመለስ የገባው የሚመስለው የሽብር ቡድኑ እኔም አልመጣበት እናንተም አትሻገሩበት ያለ ይመስላል። ለምን ካሉ ዘመን የማይለያያቸው ዜጎች የሚገናኙበትን ድልድይ አፍርሶታልና። የሽብር ቡድኑ የሚጠላውን ሕዝብ ይጎዳልኛል ብሎ ያሰበውን የትኛውንም እኩይ ሥራ ያደርጋል። የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ሕወሃት ድልድዩን ያፈረሰው አማራዎች ወደ ትግራይ እንዳይሻገሩ፣ ትግራዮችም ወደ አማራ እንዳይሻገሩ፣ መሻገሪያ አጥተው እንዳይነጋገሩ እና ተቆራርጠው እንዲቀሩ በማሰብ ነው ይላሉ። ሕወሃት በሕዝብ ጠብ ውስጥ ሰርግ ይሰርጋል፣ ድግስ ያሞቃል፣ ከበሮ አንስቶ ይደልቃልና። የቆራሪት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፋኖስ አብርሃ አሸባሪው ሕወሓት መሠረተ ልማቶችን ማፍረስ መገለጫው እንደኾነ ነው የተናገሩት። ለእኛ ያልተመቸች ኢትዮጵያ ትፍረስ፣ መሠረተ ልማቶቿም ይፍረሱ እንደሚልም ተናግረዋል። የአማራና የትግራይ ሕዝብ የሚገናኝበትን ድልድይ ማፍረሱንም ገልፀዋል። ዜጎች ዳግም እንዳይገናኙ፣ ተለያይተው እንዲኖሩ ስለሚፈልግ ያደረገው ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል። በሽብር ቡድኑ የፈረሰው የተከዜ ድልድይ ለትግራይ ሕዝብ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው እንደኾነም ገልጸዋል። ድልድዩን አፍርሶ ፈረሰብኝ ብሎ እንደሚጮህም ነግረውናል። ሕወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ ፍፁም ጥላቻ ቢኖረውም የአማራ ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ላይ አይነሳም፣ ሁለቱ ሕዝቦች በቀደመው ፍቅራቸው ይቀጥላሉ፣ ድልድዩ ይሠራል፣ ሕወሓት ግን እንዳይነሳ ኾኖ ይመከታል ነው ያሉት። ቀደም ሲል የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ወደ መናገሻቸው ጎንደር እንዳይሄዱ፣ ጎንደርን ትተው ወደ ሽሬ እንዲሄዱ በማሰብ አሁን ያፈረሰውን ድልድይ ሠርቶት እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው እንደዛም አስቦ ድልድዩ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጠቃሚ ነበር ብለዋል። አሸባሪው ሕወሓት የወልቃት ጠገዴን ሕዝብ አሁንም ጎንደር ገበያ ሳይገበይ እንዲኖርና ሽሬና ሌሎች የትግራይ ከተሞች እየገበየ ማንነቱን እንዲቀይር የሠሩት ሥራ አልሳካ ሲል ድልድዩን ማፍረሳቸውን ገልጸዋል። አሸባሪው ሕወሓት ከራሱ ዓላማ ውጭ ለሕዝብ የሚጠቅሙ መሠረተ ልማቶችን እንደማይተውም ተናግረዋል። ዓላማውን ያሳካልኛል ብሎ እስካሰበ ድረስ የትኛውንም ነገር ከማፍረስ ወደኋላ አይልም። የቆራሪት ከተማ ነዋሪ መሪጌታ ፍሬው ተረፈ ስለ ድልድዩ መፍረስ ሲናገሩ “በድልድዩ መፍረስ አትገረሙ፣ የማትፈርሰውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳ ቡድን መኾኑን ዘነጋችሁትሳ? ድልድይ ስላፈረሰ ባሕሪው ነው እና አይገርመንም፣ ሀገር ለማፈረስ ስለሚሠራ፣ ራሱ አፍርሶ አፈረሱት ይላል” ነው ያሉት፣ የሕወሓት የሽብር ቡድን በወልቃይት ሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሰ መኾኑን ያስታወሱት መሪጌታ ፍሬው ዛሬም እንደ ትናንቱ ዜጎችን ለማሰቃየት ዳግም ጦርነት መጀመሩን ነው የተናገሩት። ድልድዩን የሰበረው ለፖለቲካ ፍጆታ መኾኑንም ገልጸዋል። አሸባሪው ሕወሓት ለየትኛውም ሕዝብ ሊኾን የማይችል እኩይ ቡድን መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ለዓመታት መስፈሪያ የሌለው በደል ሲፈጽም መኖሩን ነው የተናገሩት። በሽብር ቡድኑ የፈረሰውን ድልድይ ተመለከትኩት። መካከሉ ላይ ተመትቶ ፈርሷል። ድልድዩ ለሀገር ልማት ፣ ለተከዜ ውበት ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል የክፉዎች እጅ አረፈበት፣ ታላቁን ወንዝ የሚያልፈው ረጅም ድልድይ ተሰበረ። ሁሉም ያስገርማል፣ ለዓመታት አንድም ቀን መልካም ነገር አለመሥራት። ግን ማዕበል የሚያሻግሩ ድልድዮች ይሠራሉ፣ ድልድይ የሚያፈርሱ፣ ሕዝብን የሚያምሱ ጠላቶች ላይጠገኑ ይመከታሉ። ያን ጊዜ ወዳጆች ይገናኛሉ ፣ በአንድ ላይ ይስቃሉ ሲል አሚኮ ዘግቧል። ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply