የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት በነገው ዕለት እንደሚፈጸም ተገለጸ

ዕረቡ መስከረም 18 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት በነገው ዕለት ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ አራት ኪሎ በሚገኘው በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጿል።

ለዚሁ የቀብር ሥነ ስርዓት የተቋቋመው ኮሚቴ ቃል አቀባይ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ሰይፉ ፋንታሁን ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ (ቪ ኦ ኤ) እንደገለጸው ከሆነ፤ የድምጻዊው የቀብር ሥነ ስርዓት በነገው ዕለት በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል የሚፈጸም ይሆናል።

ከቀብር ሥነ ስርዓቱ አስቀድሞ ከቀኑ 6:00 ሰዓት በወዳጅነት አደባባይ የክብር ሽኝት ፕሮግራም እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

ማዲንጎ አፈወርቅ ትናንት ማክሰኞ መስከረም 17 ቀን 2015 ጠዋት 1፡30 አካባቢ፤ ለሐኪሙ ስልክ በመደወል ወደ ክሊኒክ እንደሄደና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ የግል ክሊኒክ የህመም ማስታገሻዎችን እና ሌሎች መድኃኒቶችን ወስዶ እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፤ ማዲንጎ ከረፋዱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ህይወቱ ማለፉን ገልጿል።

የድምጻዊው አስክሬን ሕይወቱ ካለፈበት የግል ክሊኒክ ወደ አቤት ሆስፒታል ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ በቀረበለት አቤቱታ መሠረት የድምጻዊውን ሞት መንስኤ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል።

አዘዞ ተወልዶ በደብረታቦር ከተማ ያደገውና ከ 1980ዎቹ አጋማሽ አንስቶ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጉዞ ከተቀላቀሉ ድምፃውያን መካከል በቀዳሚኒት የሚጠቀሰው ማዲንጎ አፈወርቅ፤ በ1987 “ስያሜ አጣሁላት” በተሰኘው ቀዳሚ የአልበም ሥራው ከሙዚቃ አፍቃሪያን የተዋወቀ ሲሆን፤ በ1990ዎቹ ‹‹አይደረግም›› እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት በፊት ‹‹ስወድላት›› የተሰኙ ተወዳጅ የሙዚቃ አልበሞችን ወደ አድማጮች አድርሷል።

በተጨማሪም በበርካታ ነጠላ ዜማዎቹ በመስራት በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምጻዊ ማዲንጎ፤ አራተኛ አልበሙን ለአድማጮች ለማድረስ በመስራት ላይ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

The post የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት በነገው ዕለት እንደሚፈጸም ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply