የተጋነነ ጭማሪ ባይታይም የበዓል ገበያ ቀዝቅዟል

የፍየል ዋጋ አይቀመስም – የበግ ቅናሽ አሳይቷል

የትንሳኤ በዓል የገበያ ዋጋ ከገና በዓል የገበያ ዋጋ አንፃር መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱን ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ፡፡ የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ትልልቅ የገበያ ቦታዎችን ከቃኙ በኋላ ባገኙት መረጃ ነው የበዓል ግባቶች የዋጋ ሁኔታ  መጠነኛ  መረጋጋት ማሳየቱን ማረጋገጥ የቻሉት።  ነጋዴዎችና ሸማቾች እንደገለፁት፤ ለገና በዓል ገበያ የ1 ኪሎ የሽንኩርት ዋጋ 150 ብር የነበረ ሲሆን ሰሞኑን አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ55-60 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ለገና 11 እና 12 ብር የነበረው የፈረንድ እንቁላል አሁን በዘጠኝና በ10 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ምንም እንኳን በዓሉ ከመቃረቡ በፊት የፈረንጅ እንቁላል ሰባት ብር ከሀምሳ ሲሸጥ የቆየ ቢሆንም አሁን ከ9-10 ብር መሸጡ ከገናው በዓል የዋጋ ሁኔታ አንፃር የተሻለ መሆኑን ሸማቾች ገልፀዋል። በስድስት ኪሎ፣ በመገናኛው ሾላ፣ በሰሜን ማዘጋጃው ሾላ ገበያ፣ በሀይሌ ጋርመንትና በፈረንሳይ አካባቢ በሚገኙ ገበያዎች የተዘዋወሩት የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች ለመቃኘት እንደሞከሩት፣ የዓመት በዓል ፍጆታዎች ዋጋ ከቦታ ቦታ መጠነኛ ለውጥ እንዳለው ለመታዘብ ችለዋል፡፡
በ6 ኪሎ አትክልት ተራ ቀይ ሽንኩርት 60 ብር፣ ካሮት 80 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 360 ብር፣ ሎሚ በኪሎ 250 ብር፣ ድንች 40 ብር እየተሸጠ ሲሆን ፈረንሳይ አካባቢ ትልቁ የወላይታ ዶሮ ከ1 ሺህ 300 እስከ 1 ሺህ 700 ብር ድረስ ለገበያ ቀርቧል፡፡ 5 ሊትር ኦማር ዘይት 1 ሺህ 150 ብር እየተሸጠ ሲሆን የ100 ብር ጭማሪ አሳይቷል።
መጠነኛና አነስ ያሉ የፈረንጅ ዶሮዎች ከ1 ሺህ 100 ብር ጀምሮ እየተሸጡ ሲሆን፣ የዳቦ ዱቄት አንደኛ ደረጃው በኪሎ 1 መቶ ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ አንደኛ ደረጃ የሸኖ ቅቤ ለጋው 900 ብር መካከለኛው 800 ብር እንዲሁም በሳሉ 690 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በመገናኛው ሾላ የገበያ ቅኝታችን ደግሞ  አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ40-70 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት ከ350 እስከ 400 ባሮ ሽንኩርት በኪሎ 45 ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ በተለይ ነጭ ሽንኩር በአዘቦት ቀናት ሲሸጥበት ከነበረው ዋጋ በጣም መወደዱን ሸማቾች ተናግረዋል።  በዚሁ በመገናኛ ሾላ ገበያ የሀበሻ ዶሮ ከ1 ሺህ 200 እስከ 1 ሺህ ሰባት መቶ ብር ሲሸጥ፣ የፈረንጅ ዶሮ ከ1 ሺህ 100 እስከ 1 ሺህ 600 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ መካከለኛ የፈረንጅ ዶሮ ከ800 እስከ 850 ብር እየተሸጠ መሆኑንም የሾላን ገበያ የቃኘው ሪፖርተራችን ገልጷል፡፡
በፈረንሳይ የበዓል ገበያም ሆነ በሾላ ገበያዎች  ዶሮ እዚያው ገዝቶ እዚያው የማሳረድ ባህል እየተስፋፋ ሲሆን ምንም እንኳን በቅኝታችን ወቀት ገና ፆሙ ያልተፈታ  ባለፈው ገና አንድ ዶሮ አርዶ ለመገንጠል ከ3-5 ደቂቃ እንደሚፈጅና ለአንድ ዶሮ 100 ብር ያስከፍሉ እንደነበር አረጋግጠናል፡፡ በሾላ ደግሞ ከ50 ብር እስከ 150 ብር ለዶሮ አራጅ እንደሚከፈል ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
በሾላ ገበያ የሸኖ ቅቤ ለጋው በ950 ብር የሚሸጥ ቢሆንም ሲሆን፤ መካከለኛው 850 ብር፤በሳል ቅቤ በ750 ብር እየተሸጠ ነው። በበዓል ገበያ ቅኝታችን በሾላ ገበያ ካገኘነው የበዓል ግብአት ውስጥ ለጠላ የሚሆን የተመጣጠነ ውህድ ዱቄት (ጌሾ ብቅል፣ አሻሮ ተዘጋጅቶ የተቀላቀለ) ሲሆን፤ 1 ኪሎ ግራም የታሸገ የጠላ ምጥን 200ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከጠላ ምጥኑ ጎን ለጎን ደግሞ አልኮል የሌለውና ከገብስ ብቻ የሚዘጋጀው “ኬኔቶ” (መውደድ) ለሚባለው መጠጥ የሚውል አረር ተደርጎ የተቆላ ገብስ በ1 ኪሎ ግራም መጠን ታሽጎ እንዲሁ በ200 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
አዲስ አድማስ ሀይሌ ጋርመንት አካባቢ የሚገኘውን የበግና የፍየል ገበያ ለመቃኘትም ሞክሯል፡፡ በዚሁ ቅኝት ምንም እንኳን እንደቀድሞዎቹ የበዓላት ድባብ የደመቀና የደራ የገበያ እንቅስቃሴ ባናስተውልም፣ ነጋዴዎች ግን ከቀደሙት በዓላት የዋጋው ሁኔታ ጥሩ የሚባል መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ ከገበያው በበዓሉ ዋዜማ እየደመቀ እንደሚሄድና የሸማቹ መጠን ይጨምራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
በዚሁ የቁም እንስሳት የግብዓት ስፍራ አነስ የሚል በግ ከ6 ሺህ ብር ጀምሮ እየተሸጠ ሲሆን መካከለኛ መጠን ያለው ከ8-10 ሺህ ሙክት በግ ከ12 እስከ 15 ሺህ ብር እየተጠራበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአሁኑ የበዓል ሰሞን የበግ ዋጋ ካለፈው ዓመትም ሆነ ካለፈው ገና የበግ ዋጋ አንፃር ቅናሽ እንዳለው ነው ነጋዴዎች የሚናገሩት አምና የመካከለኛ በግ ዋጋ 15 ሺህ ብር እንደነበር በማስታወስ፡፡
ዘንድሮ የፍየል ዋጋ ብቻ የሚቀመስ አይደለም የሚሉት ነጋዴዎ ትልቅና ሙክት የሚለው ፍየል እስከ 45 ሺህ ብር እየተጠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በካራሎ የቁም ከብት እንስሰሳት ቅኝት ያደረጉት የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች በዚህ ገበያ የበሬ ዋጋ ምን ያህል ነው በማለት ነጋዴዎችን ገዢዎችን ያነጋገሩ ሲሆን ከ80 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ባለው የዋጋ መጠን እንደየአይነታቸውና እንደየመጠናቸው እየተሸጡ ነው፡፡ አነስተኛ የሚባለውና ከጥጃ ከፍ ያለው ወይፈን 30 ሺህ ብር እየተባለ ነው፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የፀጥታ ችግር በሬ በግ፣ ዶሮና ፍየል እንደልብ ወደከተማ ለማምጣት አስቸጋሪ በመሆኑ ለገበያው መቀዛቀዝ አንዱ ምክንያት ሲሆን ከኑሮ ውድነቱ የተነሳ የሸማቹ የመግዛት አቅም በመዳከሙ ሌላው ለበዓል የገበያ ድባብ እንደምክንያት ተጠቅሷል በሸማቾችና በነጋዴዎች ከላይ የተጠናቀረው የገበያ ቅኝት ባለፈው ረቡዕና ጋዜጣው ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሀሙስ ማታ ድረስ የተደረገ መሆኑን እየገለፅን ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን እንመኛለን፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply