
የቱን ትቶ የትኛውን ማንሳት እንደሚቻል ግራ ይገባል። መሽቶ በነጋ ቁጥር አጀንዳ ተፈልፍሎባት የምታድር ሀገር ሆናለች። ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን! መጋቢት 06 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ አሁን አሁንማ የአጀንዳ ማምረቻው ትልቁ ፋብሪካ መንግስት ሆኗል። ስራውን ትቶ ህዝብን የሚያስጨንቅ፡ በስጋት የሚወጥር፡ እረፍት የሚነሳ፡ ህይወት የሚያመሰቃቅል አጀንዳ በየደቂቃው ማምረት ላይ ተጥዷል። አንዳንዴ ራሳቸው የበተኑትን አጀንዳ ዘንግተውት መልሶ ሲጠልፋቸው እያየን ነው። የህዝብ ግንኙነት ስራቸው ደግሞ በአማተር ኮሚኒኬተሮች እጅ ላይ መውደቁ ምን ዓይነት መልዕክት ለህዝብ መድረስ እንዳለበት እንኳን ግልጽ አቅጣጫ የለም። እንደእነዶ/ር ለገሰ ዓይነት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የበረከቱና ወሬ እየለቃቀሙ የሚውሉ ሰዎች ከላይ ተቀምጠው ”በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እያሉ የሚያዝጉና የሚያላዝኑ መሆናቸውን እንደስራ ቆጥረውት ስናይ ግዴለም እዛ ቤት ያለው በሽታ የማይድን ካንሰር ሆኗል ብለን ድምዳሜ እንድንሰጥ ያደርገናል። አዲስ አበባ ላይ የሚታየውን ትርምስ ብቻ ብንወስድ ኢትዮጵያችን በሰላም ውላ የምታድርም አትመስልም። በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የአዲስ አበባ ሞግዚት ተብላ የተሰየመችው ሸገር ከተማ አዲስ አበባን ትንፋሽ አሳጥታ ነፍሷን ሲጥ አድርጋ ልትገላት ነው። ነባር መንደሮች በዘመቻ እየፈረሱ ነው። ማንነትን መነሻ ያደረገው መጠነ ሰፊ ማፈናቀል ተራ አጀንዳ ሆኗል። መብራት ለአዲስ አበቤው ብርቅ ከሆነ ሰነባብቷል። የድንጋይ ዳቦ ዘመንን አዲስ አበባ እየኖረችው ነው። ባጃጅ እንኳን ተነፍጋ ወደሙዚየም የገባው የጋሪ ትራንስፖርት የጀመሩ መንደሮች እንዳሉ እየሰማን ነው። ጤፍና ስንዴ እንደ ወርቅና አልማዝ በቀላሉ የማይገኙ ውድ ምርቶች ሆነዋል። ሸገር ከተማ ለአዲስ አበባ የደገሰችላትና ገና ወደ መሬት ያልወረደው እቅድ ነገ ከነገ ወዲያ አዲስ አበባ የምትባል ከተማ ድሮ ነበረች ብለን በታሪክ የምናስታውሳት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የአዲስ አበባ ነገር ይጨንቃል። እውነት ለመናገር የኦሮሞሚያ ብልጽግና የደቀነው አደጋና አዲስ አበባን ዒላማ ያደረገው ኢትዮጵያን የማወላለቅ ዘመቻ እንቅልፍ የሚነሳ ነው። ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ ለምክር ቤታቸው ያደረጉት ንግግር ላይ መንግስትን ለመገልበጥ አዲስ አበባ ላይ ሴራ እየተጎነጎነ ነው፡ ይህን ደግሞ ከክፍለሀገር የሚገቡ ሰዎች ናቸው የሚጎነጉኑት ሲሉ ተናግረዋል። የአማራ ተወላጆችን ወደአዲስ አበባ እንዳይገቡ የተደረገበትን ፋሺስታዊ ውሳኔ ምክንያታዊ ለማድረግ እንደሆነ ይገባናል። የሀኪም ቤት ቀጠሮ ያላቸው አሮጊት እናት፡ አቅመ ደካማ አዛውንት ሳይቀር እንዳይገቡ የተደረገው እነዚህም መንግስት ሊገለብጡ ነው ከሚል ፍርሃት ከሆነ የራስን ፍርሃት መመርመር እንጂ የባርነትን ዘመን መልሶ ባመጣው ”ዘርና ቀለም እየለዩ” የመንቀሳቀስ መብትን በመንፈግ አይደለም። ከልክ በላይ ሰውን መግፋት ጥሩ አይደለም። ሁሉም ነገር ለከት አለው። ጭቆናን ተጠይፈን ጫካ ገባን ያሉ የትላንት ነጻ አውጪዎች ዛሬ ዙፋኑ ላይ ሲቀመጡ የለየላቸው ጨቋኝና ጨፍላቂ ለመሆን ሲጣደፉ ”ሟች ሊሞት አከባቢ እንዲህ ያደርገው ነበር” የምትለዋን ቀላል ብሂል ልናስታውስ እንገደዳለን። የኦሮሚያ ብልጽግና ህወሀትን የሚያስከንዱ፡ በእጥፍ የሚበልጡ ዘረኛና ከፋፋይ አጀንዳዎችን ይዞ ሀገር ካልመራሁ እያለ ሲደናበር እያየን ነው። ኢፈርት የተባለውን የህወሀት በዘረፋ የደለበ ድርጅትን የሚያስንቁ የኦሮሚያ ኩባንያዎች በየሰከንዱ እየተፈለፈሉ ነው። አንዳንድ ከእነሱ ወገን ያልሆኑ ባለሀብቶች የህወሀት ዘመን ይማረን እያሉ እንባቸውን ወደሰማይ መርጨት መጀመራቸውን መስማት ከጀመርን ቆየን። አሁን ኢትዮጵያ ላይ ገኖ የሚታየውና እዚህም እዚያም የሚንጎማለለው አይን ያወጣ፡ በዘርና በጎሳ የተደራጀ ዘረፋ ነው። የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ የወቅቱ መፈክር ሆኗል። እፍረት የለም። ይሉኝታ የለም። ምስኪኑ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብሮ ይሰቃያል። በስሙ ስልጣኑን የጨበጡት ባለጊዜዎች ዘረኝነትን እየጋቱት፡ ጭቆናን እየዘመሩለት፡ ከታሪክ እስረኝነት እንዳይላቀቅ ሰንሰለቱን እያጠበቁለት እነሱ አይናቸውን ጨፍነው በዘረፋው ላይ ተጠምደዋል። አንድ እዚህ ባህርማዶ የማውቀው የኦሮሞ ምሁር ሀገር አማን ነው ብሎ ለውጡን ለማገዝ ወደ ሀገር ቤት ገባ። ስልጣን ሰጡት። ስድስት ወርም አልቆየ። ተመልሶ መጣ። ምነው? አልኩት። የእኔ ወንድም ሀገር በቁሟ እየተዘረፈች ነው። እንዲህ አንድ ያደረጋቸው የህዝብ አጀንዳ እንዳይመስልህ። ከእግር ጥፍራቸው እስከራስ ጠጉራቸው ድረስ የዘረፋ ባህር ውስጥ ተዘፍቀዋል። የእነሱ ማህበር አባል ካልሆንክ ያጠፉሃል። የኦሮሞ ብልጽግና ነቅዟል። ዘረኝነትን ከፊት አስቀድሞ ከጓዳ ዝርፊያውን ተያይዞታል። ጎመን በጤና ብዬ ተመለስኩ።” “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post