የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌት በስኬት መከናወኑ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲዉ ዘርፍ አዎንታዊ ሚና እንዲኖራት እንደሚያደርግ የፖለቲካ ተንታኞች  ገለፁ፡፡

የህዳሴ ግድብ ሁለተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ በጎረቤት ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በመላዉ አፍሪካ እና በአለም አቀፍ መድረክ ትልልቅ የዲፕሎማሲ ሚና እንድትጫወት እንደሚያደርጋት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ አለሙ አራጌ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ግድቡ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር የሚፈጥር እና የኢትዮጵያ ተሰሚነትን እንዲጨምር የሚያደርጋት ሲሆን በአፍሪካ የሚኖራትን ተሰሚነት በመያዝ በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ትልቅ ኃይል እንዲኖራት እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

አቶ አለሙ አክለዉም እየደረሰብን ያለው አለም አቀፍ ጫና እንዲቀንስ በህዳሴዉ ግድብ  ያሳየነዉን አንድነት በሀገር ዉስጥ ሰላማችንም ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሌላኛዉ ሀሳባቸዉን ለአሐዱ የገለፁት ተንታኝ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አሰፋ ካሳ ናቸዉ ፤ ከዉሀ ሙሌት በፊት የነበረዉ አለም አቀፍ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልነበረ ገልፀዉ ኢትዮጵያ ከዉሃ ሙሌቱ በኋላም የያዘችዉን የዲፕሎማሲ መንገድ አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል፡፡

አለም አቀፍ ተቋማት ከሚያደረሱት ተፅእኖ አንፃር የኛ ዲፕሎማሲ ክፍተት ያለዉ ነው ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን እንድታሳካ እና በአቋሟ እንድትፀና ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

በዲፕሎማሲዉ ዘርፍ አሸናፊነቷ እየታየ እንደሚገኝ እና የዲፕሎማሲ አቅሟ በጨመረ ቁጥር አለም አቀፍ ተፅዕኖው  እየቀነሰ  እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡

አቶ አሰፋ አክለዉም ኢትዮጵያ ያላትን እዉነት የማስረዳት አቅሟን ማሳደግ እንደሚገባት እና ሀገራዊ አንድነቷን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስረግጠዋል፡፡

ቀን 16/11/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply