የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ መንግስት እልባት እስኪሰጥ ድረስ ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ተማሪዎች ማህበር አተማ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም…

የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ መንግስት እልባት እስኪሰጥ ድረስ ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ተማሪዎች ማህበር አተማ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ተማሪዎች ማህበር አተማ ከጥቅምት 15-17 አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ማካሄዱንና በስኬት ማጠናቀቁን ገልጧል። የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) ጠቅላላ ጉባዔውን የተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙበት አስቸኳይ ጉባኤውን አካሂዷል። ጉባኤው ከጥቅም 15-17 ቀን 2013 ዓ.ም በባህርዳር ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በተለያዩ የአማራ ተማሪዎች እና ህዝቦች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጓል። ከትናንት የቀጠለው የአማራ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ መፈናቀል፣ መታገት፣ መገደልና መሰል ማሳደዶችን ለማስቆምና መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ አለፍ ሲልም መንግስት የመጀመሪያ ስራው በሆነው የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ስራውን ባለመወጣቱ በኦሮሚያ ክልል፣በጉራፈርዳ፣ በመተከል በግፍ የተገደሉና የተፈናቀሉ አማራዎችን ጉዳይ በማንሳት ተወያይቷል። ማህበሩ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በጥቃት ምክንያት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ለማስመለስና የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከተ ከመንግሥት ጋር ያደረገውን ውይይት የገመገመ ሲሆን በቀጣይ የትምህርት ዘመን ከትናንት የቀጠለው መፈናቀልና መታገት ማስቆም በሚቻልበት ዙሪያም መክሯል። በመሆኑም መንግስት የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ወደ መደበኛ ትምህርት ለመመለስና ፈተና ሳይፈተኑ የተፈናቀሉ ተማሪዎች ተገቢው ማካካሻ ተሰጥቷቸው ፈተናውን ተፈትነው ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ጠይቋል። በተጨማሪም መንግስት አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታየውን የአማራን ተማሪ ኢላማ ያደረገ ማንነት ተኮር ጥቃት ማስቆም በሚችልበት ቁመና ላይ መሆኑን ለመላው ማህበረሰብና ለተማሪ ወላጆች እንዲያረጋግጥና ሙሉ ሀላፊነት እስከ ዋስትና እንዲወስድም ጠይቋል። አተማ የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይም መንግስት እልባት እስኪሰጥ ድረስ ጥያቄችን አጠናክረን በምንቀጥልበት ጉዳይ ላይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡንም አስታውቋል፡፡ የአማራ ተማሪዎች ማህበር ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርስቲዎች በሚነሱ የዘር ተኮር ጥቃቶች ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ሁኔታ የተመለከተ ሲሆን በአማራ ትውልድ ቀጣይ እጣፈንታ ላይ ‹Elite Genocide› እየተፈጸመ በመሆኑና በቶሎ ማቆም እንዳለበት ያምናል ብሏል አተማ በመግለጫው። በዚህም መላው የአማራ ህዝብ የተማሪዎች ሁለንተናዊ ደህንነት ተጠብቆ ትምህርታቸውን መማር ይችሉ ዘንድ አስፈላጊውን ሁሉ ግፊት እንድታደርጉ ሲል ነው የአማራ ተማሪዎች ማህበር ጥሪውን ያቀረበው። ዘመቻ ሚኒልክ የመጽሃፍ እና የደብተር ማሰባሰቡ ዘመቻ (አንድ ደርዘን ደብተር እና መጽሀፍ ማሰባሰብ) በይፋ የዘጋ ሲሆን የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያረጉ የነበሩ የተለያዩ አካላትና የተሻለ ተሳትፎ ላረጉ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና ሰጧል። በመጨረሻ በአማራ ህዝብ ላይ ማለትም በመተከል ፣ ጉራፈርዳ ፣ አጣዬ፣ ከሚሴ፣ በሻሸመኔ እና በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለውን ግልጽ የሆነ የአማራን ዘር የማጥፋት ወንጀልን መንግስት በስሙ ከመጥራት ጀምሮ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣ በጥብቅ እናሳስባለን ብሏል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply