የቴዎድሮስ ተሾመ “ስለ እናት ምድር” ፊልም ቅዳሜ ይመረቃል

የቴዎድሮስ ተሾመ “ስለ እናት ምድር”  ፊልም  ቅዳሜ ይመረቃል
• በፊልሙ ላይ 30ሺ ሰዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል
በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ የተሰራውና “ስለ እናት ምድር” የተሰኘው ዶክመንተሪ ፊቸር ፊልም፣ ከነገ ወዲያ ቅዳሜ ከቀኑ 8 ሰዓት በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡
አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በዛሬው ዕለት በግዮን ሆቴል፣ ግሮቭ ጋርደን ወክ፣ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገረው፣ በፊልሙ ላይ ሰላሳ ሺ ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ የሦስት ሰዓት እርዝማኔ እንዳለውና ታሪኩንም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ያደረገ መሆኑን ጠቁሟል።
ፊልሙ በአሜሪካን ሀገር ሎሳንጀለስ ከተማ በተካሄደ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ሁለት መቶ ከሚሆኑ ፊልሞች ውስጥ ከተመረጡ ሦስት ፊልሞች አንዱ ለመሆን እንደበቃ አርቲስት ቴዎድሮስ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
ፊልሙ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ አላማጣ፣ ዞብል፣ ወልድያ፣ ቆቦ፣ ኮምቦልቻ እንዲሁም ጅማ ከተማና ደነባ በተሰኙ ቦታዎች ላይ የዘመኑ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ በሆነው 12 k የተሰኘ የቪዲዮ ካሜራ እንደተቀረፀ የተገለፀ ሲሆን፤ ቀረፃውም ዓመት ከስምንት ወር እንደፈጀ ተብራርቷል።
በፊልሙ ላይ በቲክቶክ ስራዎቿ የምትታወቀው ፅጌ ሮያል መሪ ተዋናይ ስትሆን፣ አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱም ተውኖበታል ተብሏል። በዚህ ፊልም ላይ ከሆሊውድና ከቦሊውድ የመጡ ባለሙያዎችም እንደተሳተፉበት ተነግሯል፡፡
“ስለ እናት ምድር” የተሰኘው ፊልም ከምርቃቱ በኋላ በሁሉም ሲኒማ ቤቶች ለዕይታ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply