የትምህርት ሚኒስትሩ እና ወ/ሮ አዳነች በአዲስ አበባ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስጀመሩ

የትምህርት ሚኒስትሩ እና ወ/ሮ አዳነች በአዲስ አበባ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስጀመሩ።

በአዲስ አበባ ከተማ የ8ኛ እና የ12 ክፍል የገጽ ለገጽ የማካካሻ ትምህርት ተጀምሯል።

የመማር ማስተማር ሂደቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እና ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዳግማዊ ሚኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት በመገኘት በይፋ አስጀምረውታል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የመምህራንን ጫና ለመቀነስ እኔም አስተምራለሁ የሚለውን ንቅናቄ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በማስተማር አስጀምረዋል።

በትምህርት ቤቱ በሚወጣ መርሃ ግብር መሰረት ለ45 ቀን የማስተማር ስራውን እንደሚከውኑ ገልፀዋል።

ሌሎችም በመምህርነት ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በመምህራን ላይ የሚኖረውን ጫና ለመቀነስ በበጎ ፍቃደኝነት የመማር ማስተማሩን ሂደት እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ተማሪዎች ከጤና ባለሙያዎች እና መምህራን የሚሰጣቸውን ምክር እና አቅጣጫ በአግባቡ እንዲተገብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲሳካ ከዩኒፎርም ጀምሮ የመማሪያ ቁሣቁሶች እንዲሁም የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ተማሪዎች በትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው ከኮቪድ -19 በተጨማሪ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎል ከሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም አካላት እንዲርቁ ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በኮከበ ጽባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የገጽ ለገጽ ትምህርቱን በይፋ አስጀምረዋል።

The post የትምህርት ሚኒስትሩ እና ወ/ሮ አዳነች በአዲስ አበባ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስጀመሩ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply