
የትራንስፖርት ባለስልጣኑ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላልተወሰነ ግዜ ከስራ ውጭ እንዲሆኑ እገዳ መጣሉ የኑሮ ውድነቱን ከግንዛቤ ያላስገባ ነው ተባለ! መጋቢት 01 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ የካቲት 30/2015 ዓ/ም ጀምሮ ላልተወሰነ ግዜ ከስራ ውጭ እንዲሆኑ እገዳ መጣሉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት ከግንዛቤ ያላስገባ ነው ሲሉ አሽከርካሪዎች ለአማራ ድምፅ ገለፁ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን በተሻለ መልክ ለመምራት የሚያስችል የአሰራር ማሻሻያ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን በመግለፅ፡ የማሻሻያ ስራው ተጠናቆ እንዲሁም የአገልግሎቱ አስፈላጊነት በዝርዝር ተጠንቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ከዛሬ የካቲት 30/2015 ዓ/ም ጀምሮ በከተማዋ በየትኛውም አከባቢ ላልተወሰነ ጊዜ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት የታገደ መሆኑን አስታውቋል። የአማራ ድምፅ ያነጋገራቸው በከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አሽከርካሪዎች እንደገለፁት፡ የተላለፈው መመሪያ ለሀገሪቱ ህዝብ ከባድ ፈተና የሆነው የኑሮ ውድነትን ታሳቢ ያላደረገ ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ብዛታቸው ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ሲሉ አሽከርካሪዎቹ ገልፀዋል። ከእነዚህ መካከል በሚያገኙት የቀን ገቢ ብቻ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ በርካታ አሽከርካሪዎች እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን የተጣለው እገዳ እነዚህን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ነው ተብሏል። የባለ ሥስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላልተወሰነ ግዜ በመታገዳቸው ከአሽከርካሪዎቹ በተጨማሪ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነው የከተማዋን ነዋሪ ላልታሰበ ወጭ እንደሚዳርግም ተመላክቷል። መመሪያው ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከመተላለፉም በላይ ለምን ያህል ግዜ እንደሚቆይ አልተገለፀም ሲሉ ለአማራ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡት አሽገርካሪዎቹ፡ ይህ አይነት አካሄድ ህዝብን ለአመፅ የሚገፋፋ መሆኑንም ገልፀዋል። ዘገባው የአማራ ድምፅ ነው ። “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post