በ2011 ዓ.ም ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ምስረታውን ያደረገው ባይቶና የመጀመሪያ ጉባኤውን ቅዳሜና እሁድ ጥቅምት 17 እና 18 በማካሄድ ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም በ2012 ዓ.ም ጥቅምት 23 የመስራች ጉባኤ ያካሄደ ቢሆንም በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሳይሰጠው መቅረቱ ይታወሳል፡፡
የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቀበል ፓርቲውን የማደራጀት ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሄ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ ፓርቲውን በማደራጀት ሂደት ውስጥ በርካታ እንቅፋቶች የነበሩ ቢሆንም እሱን ሂደት አልፎ ፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤውን አካሂዶ ማጠናቀቁን ገልፀውልናል፡፡
ፓርቲው የትግራይ ህዝብ ማንኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንጂ በጠመንጃ የሚፈታ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
የፕሪቶሪያውን የሰላም ሰምምነት አተገባበር መገምገሙን የገለፁት የፓርቲው አመራር፣ ስምምነቱ በተሟላ መልኩ ባለመሆኑ የክልሉ ህዝብ አሁንም በርካታ ችግሮችን እያሳለፈ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚሁ ጉዳይም ፓርቲው በቁርጠኝነት የሚታገል መሆኑን አንስተው፣ የሚመለከታቸው አካላት ላይ ጫና ለማሳደር እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ለባይቶና አባይ ትግራይ በፃፈው ደብዳቤ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተቀመጠውን መስፈርት በማሟላት የተከናወነ ባለመሆኑ ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልጾ በድጋሚ አዋጁን መሰረት አድርጎ ማካሄድ እንደሚችል መግለፁ ይታወሳል፡፡
ጥቅምት 17 እና 18 ተካሂዶ በተጠናቀቀው ጉባኤ ላይ፣ የምርጫ ቦርድ ሁለት ታዛቢዎች መሳተፋቸው የተገለፀ ሲሆን ቦርዱ የፓርቲውን ጉባኤ ተቀብሎ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ዮሴፍ ተናግረዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube
https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/video
Source: Link to the Post